በጥቅምት ወር ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሆርቲካልቸር ምርት ከ48 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፦ በጥቅምት ወር ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሆርቲካልቸር ምርት ከ48 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጥቅምት ወር ከዘርፉ የተገኘው የገቢ አፈፃፀም ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር 98 በመቶ ሲሆን ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ20 ነጥብ8 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በሚኒስቴሩ የሆርቲካልቸር ኤክስፖርት ድጋፍና ክትትል አስተባባሪ መኮንን ሰለሞን ለኢዜአ እንዳሉት በጥቅምት ወር 31 ሺህ 514 ቶን የሆርቲካልቸር ምርት ለመላክ ታቅዶ 25 ሺህ 425 ቶን ተልኳል።

በወሩ ከዘርፉ ወጪ ንግድ 49 ነጥብ 21 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 48 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት አራት ወራት ከዘርፉ ወጪ ንግድ 167 ሚሊየን ዶላር መገኘቱንም ጠቁመዋል።

ባለፉት አራት ወራት በምስራቅ አፍሪካ ተከስቶ የነበረው ቅዝቃዜ የአበቦች እድገት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በመዳረሻ ገበያ የሚቀርበውን ምርት እንዲቀንስ ማድረጉን ገልፀዋል።  

  በበጀት ዓመቱ 670 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ገልፀው፤ ይህን ለማሳካት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።     

ወደ መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ የሚሄዱ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ወለል ተግባራዊ መደረጉ በገቢው ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።   

በቀሩ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቅንጥብ አበባ ላይ ዝቅተኛ የዋጋ ወለል እንዲወጣና በአትክልትና ፍራፍሬ ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ ማሸጊያ እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

ኔዘርላንድ፣ የሳዑዲ አረቢያ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካና ጃፓን የኢትዮጵያ አበባ ምርት መዳረሻ አገራት መሆናቸውን አንስተዋል።

የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ደግሞ ወደ ጎረቤትና መካከለኛው ምስራቅ አገራት እየተላከ ነው ያሉት አስተባባሪው፥ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሆርቲካልቸር ልማትና ግብይት ስትራቴጂን ለማሳካትና ዘርፉን ለማነቃቃት አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል። 

 

 

       

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም