የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በአርባምንጭ ከተማ ታላቅ ሩጫ ነገ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በአርባምንጭ ከተማ ታላቅ ሩጫ ነገ ይካሄዳል
አርባምንጭ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፡- 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በአርባምንጭ ከተማ ታላቅ ሩጫ ነገ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የሩጫውን መረሃ ግብር አስመልክተው የክልሉ ባህል፣ኪነ ጥበብና ስፖርታዊ ሥራዎች ዘርፍ አስተባባሪዎች ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው እንደተመለከተው፤ 19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ነገ በአርባምንጭ ከተማ የሚካሄደው ታላቅ ሩጫ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።
ሩጫው “አሻራችን ለስታዲዮማችን” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊና የባህል፣ኪነ ጥበብና ስፖርታዊ ሥራዎች ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ኦላዶ ኦሎ እንዳሉት፤ ሩጫው የህብረተሰቡን አንድነት በማጠናከር ለልማት ያለውን ተሳትፎ እንዲያጎለብት ለማነሳሳት ያግዛል።
አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሩጫ መነሻውና መድረሻው ጋሞ አደባባይ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በሩጫው ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚሁ ታላቅ ትእይንት ህብረተሰቡ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊና የባህል፣ኪነ ጥበብና ስፖርታዊ ሥራዎች ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ዓለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው፤ ሩጫው በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ግንባታን በገቢ ለማጠናከር ዓላማ እንዳለውም ተናግረዋል።
የአርባምንጭ አለም አቀፍ ስታዲዮም ግንባታ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ በተፋጠነ ሁኔታ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የስታዲየሙ አጠቃላይ ወጪ በህብረተሰቡና በመንግስት የጋራ ተሳትፎ የሚገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።
"ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን በድምቀት ለማክበር በተለያዩ ዘርፎች ኮሚቴዎች ተዋቅረው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል።