አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ለማግኘቷ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ለማግኘቷ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ለማግኘቷ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ ገለጹ፡፡
እ.አ.አ በ1993 የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የደን አስተዳደር ምክር ቤት ለኢትዮጵያ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያም በምክር ቤቱ የአስተዳደር ማረጋገጫ ከተሰጣቸው ከ85 በላይ አባል ሀገራት መካከል አንዷ መሆን ችላለች፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ40 ቢሊዬን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋኗን ከ23 በመቶ በላይ አድርሳለች፡፡
የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለደን ልማት ምቹ ሥነ ምህዳር ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡
ለአየር ንብረት፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ጥቅም የሚውሉ ሀገር በቀል ዛፎች ጭምር ያሉባት መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ምክር ቤቱ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ለመስጠት ያወጣችውን ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ለማሟላት ያደረገችውን ጥረት እናደንቃለን ብለዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተራቆቱ መሬቶችን በደን ለመሸፈንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብዙ መስራቷንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የደን አስተዳደር ደረጃ ለመካተቷ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የጎላ አስተዋፅኦ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያ የደን ልማት ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትብብር እንሰራለን ብለዋል፡፡
በፎሬስት ኦፍ ዘ ወርልድ የደን አስተዳደር ቴክኒካል ኤክስፐርት ጀንስ ካንስትራፕ ኢትዮጵያ ያገኘችው የአስተዳደር ደረጃ የአካባቢ ጥበቃን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ልማት አስተዳደር ምክር ቤቱን ደረጃ ያሟለ መሆኑን ገልጸው፤ ከደን ልማት የሚገኙ ምርቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጀመረችው የደን ልማት መርኃ ግብር የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋገጠዋል፡፡