ቀጥታ፡

የተቋማትን የተልዕኮ ስኬታማነት ለማረጋገጥ የሥነ-ምግባር ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ):-  የተቋማትን የተልዕኮ ስኬታማነት ለማረጋገጥ የሥነ-ምግባር ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡ 

የፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ''ሥነ-ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማት ተልዕኮ ስኬት'' በሚል መሪ ሃሳብ በቱሪዝም ዘርፍ  አመራሮች ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡


 

ስልጠናው በቱሪዝም ዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች በውጤታማነታቸው እንዲቀጥሉ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሥነ-ምግባር ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ፍቃዱ ሰቦቃ፤ ኮሚሽኑ በሙስና መከላከል ዙሪያ ለሥነ-ምግባር ግንባታ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

የዘርፎች የሙስና ተጋላጭነትን በተመለከተ ጥናቶችን በማድረግ ለ26 ዘርፎች ስልጠናዎችን የመስጠት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የተቋማትን ስኬታማነት ለማረጋገጥ የሥነ-ምግባር ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው ለቱሪዝም ዘርፉ የሚሰጡ ስልጠናዎች የዘርፉን የሙስና ተጋላጭነት ለመቀነስ እንደሚረዱም ገልጸዋል፡፡

መንግስት በቱሪዝም ዘርፉ እያከናወነ የሚገኘው ዘመን ተሻጋሪ ስራ በሙስናና ብልሹ አሰራሮች እንዳይደናቀፍ አመራሩ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡ 

መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ማገዝና መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል ለቱሪዝም ዘርፉ የሚሰጡ ስልጠናዎች የመንግስት ጥረቶች ከግብ እንዲደርሱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡


 

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው በቱሪዝም ዘርፉ የሚከናወን ሙስና የሀገርን ገጽታ ያጠለሻል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ የዘርፉን ተጋላጭነት በማጥናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለመስራት ማቀዱ ቱሪዝም ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዲያድግ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት ሳሙኤል ሃይሉ እና ተስፋጺዮን ዮሱፍ እንዳሉትም፤ ስልጠናው በሙስና መከላከል ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል፡፡

ሙስና ለሀገርና ለህዝብ ጠንቅ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል፡፡

ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም