የተሻለ የግብይት ስርዓት እንዲኖር የህብረት ስራ ማህበራትን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የተሻለ የግብይት ስርዓት እንዲኖር የህብረት ስራ ማህበራትን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ
አዳማ ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ):- የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን በማጠናከር የተሻለ የግብይት ስርዓት እንዲኖር የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ።
የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን በከተማዋ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ከክልሎች ግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርት አቅራቢዎች ጋር ያላቸውን የገበያ ትስስር ለማሳደግ ያለመ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በመድረኩ እንዳሉት፣ የህብረት ስራ ማህበራት በከተማው ግብይትን በማሳለጥ ረግድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው።
ማህበራቱ ከክልሎች ምርቶችን በማጓጓዝ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ለከተማው ነዋሪ እያቀረቡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ማህበራቱ በከተማዋ በተገነቡ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት ግብአቶችን ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንኑ በማጠናከር የገበያ ዋጋ የሚያቃልል የግብይት ስርዓት ለመዘርጋት ማህበራቱን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።
የክልሎች የግብርናና ኢንዲስትሪ ምርት አቅራቢዎች ከከተማ አስተዳደሩ ህብረት ስራ ማህብራት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩም ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው የምርቶች ተደራሽነትን ለማሳደግ ከክልል ግብርና ቢሮዎችና ህብረት ስራ ማህበራት ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር ታልሞ ውይይቱ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
አክለውም ህገወጥ የምርት አቅራቢዎችን ለመከላከል የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን መግባባት ለመፍጠር መሆኑን ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል።
ማህበራቱን ይበልጥ ለማዘመንና የማህበራቱን የሪፎርም እቅድ ማሳካት የሚቻለው በህብረት ስራ ማህብራት መካከል ቀጣይነት ያለው ትስስር ሲኖር እንደሆነም አክለዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ፣ ውይይቱ የግብርና ምርቶች ግብይት ትስስር ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
የምርት አቅርቦት ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋፋት የተጀመረውን የእሁድ ገበያ ማጠናከርም ሊዘነጋ እንደማይገባ ጠቅሰው፤ ህገወጦችን በመከላከልና ማህበረሰቡ ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን ለመቀነስም ተከታታይነት ያለው ክትትልና ቁጥጥር ሊተገበር ይገባል ብለዋል።