የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው
ሀዋሳ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ):- ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው።
በዓሉ ለ32ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው "የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ቃል ነው።
በበዓሉ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተገኝተዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን፣ የሁሉም ክልሎች የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊዎች፣ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በመድረኩ እንደተገለጸው እንደአገር አካል ጉዳተኞችን ለማሳተፍ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም በሚፈለገው መልኩ አካል ጉዳተኞች ከአድሎና መገለል ነፃ መሆን አልቻሉም።
በትምህርት፣ በሥራ፣ በመረጃ፣ በጤና አገልግሎቶች፣ በልማት ፕሮግራሞች፣ በትራንስፖርት አና ሌሎች መሰል ጉዳዮች አሁንም መድሎና መገለል እየደረሰባቸው መሆኑ ተገልጿል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አካታችና አሳታፊ የሆኑ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የተገለጸው።
በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ባለው በዓል ላይ በአካል ጉዳተኞች አካታችነት ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚቀርቡ ተመላክቷል።
የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችም ቀኑን አስመልክተው መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።