የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ኢትዮጵያዊነት የሚጠናከርበት አንዱ መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ኢትዮጵያዊነት የሚጠናከርበት አንዱ መድረክ ነው
ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፡- የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ኢትዮጵያዊነት የሚጠናከርበት አንዱ መድረክ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፌዴራሊዝምና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ እሴታቸውን ለመገንባት ቀኑ የሚኖረው ፋይዳን በተመለከተ ኢዜአ በአሶሳ እና በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ምሁራንን አነጋግሯል።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ትምህርት መምህር አዳሙ ጅባት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር የኢትዮጵያን መልክ የምናይበት እንዲሁም ሀገራዊ አስተሳሰብ እንድንይዝ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የሚተዋወቁበት፣ ብዝሃነት እውቅና የሚያገኝበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም መስተጋብር እንዲጎለብት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
በዓሉ በየዓመቱ በዚህ መልኩ እየተከበረ መሔዱ ኢትዮጵያዊነት የበለጠ እንዲጠናከር፣ የህዝቦች ትስስር እንዲጠብቅ ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።
ፌዴራሊዝም በባህሪው በብዝሃነት ውስጥ አንድነትን ማጠናከር መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉ ብዝሃነት በአግባቡ እውቅና እንዲያገኝ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም አክለዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህር ሴኔሳ ደምሴ በበኩላቸው፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዚህ መልኩ መከበሩ ከሁሉም በላይ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ይላሉ።
እንደዚህ ዓይነት የአደባባይ ሁነቶች ሁሉም እኩል በሀገሩ ጉዳይ ላይ መወሰን እንደሚችል የሚታይበት መድረክ እንደሆነም አክለዋል።
በዓሉ አንዱ ሌላውን አክብሮ፣ ልዩነትን አቻችሎ፣ አንዱ ለሌላው እውቅና እንዲሰጥ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
በዓሉ ሕዝቦች ለወደፊት ጠንካራ ሀገርና የጋራ ማንነትን ለመገንባት እንዲሁም አብሮነትን የሚያሳዩበት እንደሆነም ተናግረዋል።
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ይከበራል።