በፕሪሚየር ሊጉ መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የሊጉ መሪ መቻል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሊጉ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ።
በዕለቱ መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 1 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም የሚያከናውኑት ጨዋታ የተመልካቾችን ትኩረት ስቧል።
በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በሊጉ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 6 ጎሎችን አስተናግዷል። መቻል በ17 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ አሁን በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈትን አስተናግዷል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ቡድኑ 7 ጎሎችን ሲያስቆጥር 6 ግቦች ተቆጥረውበታል። በፋሲል ተካልኝ የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ11 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አንጋፋ ክለቦች የሆኑት መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በ10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።በጨዋታዎቹ 11 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው ድሬደዋ ከተማ በ12 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በበኩሉ እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በስምንቱ ጨዋታዎች 6 ግቦችን ሲያስቆጥር 5 ጎሎችን አስተናግዷል። በዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና በ13 ስድስት ደረጃን ይዟል።
የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት፣ ባህርዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ መድን በ10ኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።
የ10ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ሕዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
የመቀሌ 70 እንደርታው አጥቂ ያሬድ ብርሃኑ እና የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ በተመሳሳይ አምስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በጋራ እየመሩ ነው።
ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ አጥቂ ቻርልስ ሙሲጌ እና ሌላኛው የቡድኑ የፊት መስመር ተሰላፊ መሐመድ ኑር ናስር፣ የመቻሉ ሽመልስ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ፣ ኤርትራዊው የሃዋሳ ከተማ ተጫዋች ዓሊ ሱሌይማንና የወላይታ ድቻው ያሬድ ዳርዛ በተመሳሳይ አራት ግቦች ይከተላሉ።