በመዲናዋ የግንባታ ተረፈ ምርት አያያዝና አወጋገድን ስርዓት የሚያሲዝ አሰራር ከነገ ጀምሮ ሊተገበር ነው- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፦ ከአዲስ አበባ ከተማ ውበትና ፅዳት ጋር የሚጣጣም የግንባታ ተረፈ ምርት አያያዝና አወጋገድ ስርዓት  የሚያሲዝ አሰራር ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በተገመገመበት ወቅት በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባ ገልጸው ነበር።

የግንባታ ተረፈ ምርት አያያዝና አወጋገድ በተለይም ተረፈ ምርት በተሽከርካሪ ሲጓጓዝ  የከተማዋን ገፅታና መሰረተ ልማት በማያበላሽ መልኩ መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በከተማዋ የሕገ ወጥ የግንባታ ተረፈ ምርቶች እና ግብዓቶችን ስርዓት ለማስያዝ የተዘጋጀው ማስፈፀሚያ ዕቅድ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተማ አቀፍ የልማት ስራዎች የሀገር ገፅታ እየለወጡ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ከተማዋን ውብና ጽዱ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት ጋር የሚጣጣም የግንባታ ተረፈ ምርቶች አያያዝና እንቅስቃሴ ስርዓት ማበጀት እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።

በዚህም የግንባታ ተረፈ ምርት የሚያንቀሳቅሱ የጭነት ተሽከርካሪዎችን የከተማዋን ውበትና ጽዳት በማይጎዳ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስገድድ አሰራር ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

ይህ አሰራር የመንገድና የሌሎች መሰረተ ልማቶችን ከጉዳት ለመጠበቅ፣ የተሳለጠ እንቅስቃሴና ጤናማ ከባቢ ለመፍጠር እንደሚያስችል ጠቁመው፤ አሰራሩ ሳይሸራረፍ መተግበር ይገባዋል ነው ያሉት።

የከተማ አስተዳደሩ ፅዳት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙላት ተገኝ በበኩላቸው፤ ከህዝብ ቁጥር፣ ከከተማው መስፋፋትና ኢንዱስትሪ ዕድገትን ተከትሎ የቆሻሻ መጠንና አይነት እየጨመረ ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው ቆሻሻን በወቅቱና በተደራጀ መልኩ የመሰብሰብ፣ የማስወገድና መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በግንባታ ሂደት የሚመነጩ ተረፈ ምርቶችና ግብዓት አያያዝና አወጋገድ ስርዓት የጎደለው በመሆኑ ለከተማ ውበት፣ ለእንቅስቃሴ እንዲሁም ለማህበረሰቡ የጤና ጠንቅ መንስኤ እንደሆነ አንስተዋል።

በመዲናዋ በ66 ወረዳዎች ሕገ ወጥ የግንባታ ተረፈ ምርት መከማቸቱን ያነሱት አቶ ሙላት፤ አዲሱ አሰራር እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጥ የግንባታ ተረፈ ምርት አያያዝ ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስቸል ተናግረዋል።  

የአዲስ አበባ የትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ በበኩላቸው፥ የግንባታ ተረፈ ምርት አያያዝና አወጋገድ የሚያስከትለውን መልከ ብዙ ችግር ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል።

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሮቤል ብርሃኑ፤ የከተማዋን ውበትና መሰረተ ልማቶችን በሚያበላሹ የጭነት ተሽከርካሪዎች ስርዓት ለማስያዝ እንደሚያሻ ጠቁመዋል።

አዲሱን አሰራር በቅንጅት በተሟላ መልኩ መተግበር እንደሚገባ ገልፀው፤ በተለይም በቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ በትብብር መስራት  አለብን ነው ያሉት።

የሕገ ወጥ የግንባታ ተረፈ ምርቶችና ግብዓቶችን ስርዓት ለማስያዝ የተጀመረው ንቅናቄ ለአንድ ሳምንት የሚቀጥል ሲሆን አዲሱ አሰራር ግን በዘላቂነት የሚፈጸም ነው ተብሏል።

ለትግበራውም ከከተማው ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት እስከ ወረዳ ባለው ተዋረድ የባለድርሻ አካላት ኮሚቴ መዋቀሩ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም