ልዩነቶችን በአግባቡ በማስተናገድ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት - አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ልዩነቶችን በአግባቡ በማስተናገድ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት - አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ):- በሲዳማ ክልል ልዩነቶችን በአግባቡ በማስተናገድ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ።
“ሀገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝብች ቀን በሲዳማ ክልል ደረጃ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
በዚሁ ጊዜ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት በክልሉ ልዩነቶችን በአግባቡ በማስተናገድ ሀገራዊ አንድነትና አብሮነትን ማጠናከር ይገባል።
ልዩነቶችን እንደ አቅምና ውበት በመያዝ ጠንካራ ሀገር መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከፋፋይ ትርክቶችን መታገልና ሕብረብሔራዊ አንድነትን ማጽናት ይገባልም ብለዋል።
''ትውልድን በገዥ ትርክት በማነጽና ያለንን የተፈጥሮ ጸጋ በማልማት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት መትጋት አለብን'' ነው ያሉት።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በበኩላቸው ከቀበሌ ጀምሮ በዓሉ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከበር ቆይቶ ዛሬ መጠቃለሉን ተናግረዋል።
በዓሉ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን አንስተው "ይህም የተጀመረውን ሀገራዊ ልማት በማጠናከር ብልጽግናችንን ማፋጠን የሚያስችል ነው" ብልዋል።
የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ "ቀኑ መከበሩ የተደበቁ ማንነቶችና ባህሎች እንዲወጡ አስችሏል" ብለዋል።
ይህ ደግሞ ሁሉም በተሰናሰለ መልኩ ለሀገራዊ አንድነት ያለውን ድርሻ እንዲወጣ ከማስቻል ባለፈ በቀጣይ ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በዓሉን በፍቅርና አብሮነትን በሚያሳይ መልኩ ማክበራቸውን የተናገሩት ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ብርሃኑ ጉደታ፣ ወጣቱ አንድነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት መክረዋል።
ለ19ኛው ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝብች ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ይከበራል።