መገናኛ ብዙሃን የወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የተቀናጀ የተግባቦት ስራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የተቀናጀ የተግባቦት ስራዎችን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል
ባህር ዳር ፤ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፡- የመገናኛ ብዙሃን ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የተቀናጀ የተግባቦት ስራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው የአማራ ክልል ህብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ገለፁ።
በክልሉ የህዝብ ግንኙነትንና የመገናኛ ብዙሃን አመራር አባላትን ያሳተፈና የወባ በሽታ ሥርጭትን መከላከል ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ተካሄዷል።
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ በላይ በዛብህ እንዳሉት፤ ወባን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው።
በክልሉ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ሊጥሉ የሚችሉ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የወባና ሌሎች በሽታዎች ስርጭት መቀነስ መታየቱን ጠቁመው፤ አሁንም የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ ሰፊ ርብርብ እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።
በተለይም ጠንካራ የተግባቦት ስራ በማከናወን መገናኛ ብዙሃን እያደረጉት ያለውን እገዛ ማጠናከር እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ህብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መልካሙ አብቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ በተቀናጀ መንገድ በተሰራ የወባ መከላከል ተግባር ስርጭቱ መቀነሱ ታይቷል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ 222 የወባ በሽታ ተጋላጭ ወረዳዎች ተለይተው በልዩ ክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ገልፀዋል።
አሁንም የወባ በሽታ ስርጭትን በዘላቂነት ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ መገናኛ ብዙሃን የበለጠ አጠናክረው ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ነው ያመለከቱት።
በክልሉ የወባና ሌሎች ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ህዝባዊ ሀላፊነት ይወጣሉ ያሉት ደግሞ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ናቸው።
ለዚህም ህብረተሰቡ የችግሩን ስፋት በመረዳት የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችን ማከናወን እንዲቻል የተቀናጀ የመረጃ ቅብብሎሽ ስራ በመስራት ህዝቡ በራሱ የመከላከል አቅም መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አመራር አባላትና የተቋማት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።