ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከፋኦ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ ናት - አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ገለጹ።

176ኛው የፋኦ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ በጣልያን ሮም ከተማ መካሄድ ጀምሯል።


 

በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከፋኦ ስትራቴጂክ እቅድ ጋር የሚስማማ ሀገራዊ እቅድ ነድፋ በግብርና ዘርፍ መጠነ ሰፊ ስራዎች እያከናወነች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ድርጅቱ በኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ስራ የኢትዮጵያ መንግስት እውቅና እንደሚሰጥና የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከፋኦ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከርም ዝግጁ መሆኗን አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ገልጸዋል።

176ኛው የፋኦ ምክር ቤት በስብሰባው እ.ኤ.አ. ከ2022-2031 ድርጅቱ በከለሰው ስትራቴጂክ እቅድ ላይ፣ እ.ኤ.አ. ከ2026 -2029 ስላለው የመካከለኛ ጊዜ እቅድ እንዲሁም በአስቻይና ፈታኝ ሁኔታዎች ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም