በክልሉ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ
ባህርዳር፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስገነዘቡ።
በኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር የሰብአዊ ቀውስ ምላሽና ማቋቋሚያ ፕሮጀክት በክልሉ በተከናወኑ ተግባራት ላይ በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ፣ ለእናቶችና ህፃናት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በክልሉ ሲቪክ ማህበራት ክፍተቶችን ለይተው በመንቀሳቀስ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ የጤና ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በክልሉ የእናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ሥራ የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሰዋል።
የእናቶችና ህፃናትን ጤና መጠበቅ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ይጠይቃል ሲሉም አክለዋል።
ማህበሩም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየሰጡ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶች፣ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና አገልግሎት ኬዝቲም አስተባባሪ ሲስተር አዲስ ዘመን ጫኔ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ማህበሩ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሰራ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታትም 63 ሚድዋይፈሮችን በ55 ጤና ተቋማት በመቅጠር ችግሮች እንዲቃለሉ ማድረጉን አውስተዋል።
በዚህም በጤና ጣቢያዎች አምጠው መውለድ የማይችሉ እናቶች በቀዶ ጥገና እንዲወልዱ በብቁ ባለሙያዎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።
ማህበሩ ባቋቋመው የሰብአዊ ቀውስ ምላሽና ማቋቋሚያ ፕሮጀክት በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በአፋር ክልሎች አገልግሎት እየሰጠ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈቃዱ ማዘንጊያ ናቸው።
በተለይ በአማራ ክልል ሦስት ከተማ አስተዳደሮችና በ13 ዞኖች በሚገኙ 39 ወረዳዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚድዋይፎች እጥረት ባለባቸው ጤና ተቋማት ባለሙያዎችን በመቅጠር የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ስልጠና የመስጠትና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ ከክልልና ከተለያዩ ዞኖች የመጡ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።