ቀጥታ፡

የፌዴራል ስርዓቱ ለዜጎች የሰጠውን የእኩል ተጠቃሚነት እድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ

ሳጃ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ):- የፌዴራል ስርዓቱ ለዜጎች የሰጠውን የእኩል ተጠቃሚነት እድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው አስታወቁ።

በክልሉ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል "ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በየም ዞን ሳጃ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው በዚሁ ወቅት እንዳሉት የፌዴራል ስርዓት በሀገሪቷ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ዘንድ ለዘመናት ሲነሱ የነበሩ የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በመፍታት ረገድ በጎ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡


 

ዜጎች የራሳቸውን ማንነትና ነፃነትን ባስጠበቀ መልኩ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ በማድረግ ረገድም ትልቁን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በህዝቦች መካከል የሚነሱ ፍትሐዊ የመልማትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚያስችልም ነው ያስረዱት፡፡

የፌዴራል ስርዓቱ ጠንክሮ እንዲቆም የጋራ አረዳድ መፍጠር፣ የጋራ አስተሳሰብ መገንባት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በክልሉም የፌዴራል ስርዓቱ ለዜጎች የሰጠውን የእኩል ተጠቃሚነት እድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተሳሰረ ባህላዊ እሴት ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“የበዓሉ መከበር የክልሉን ህዝብ ባህል በማስተዋወቅና ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለጋራ ለውጥ እድንተጋ ከማድረግ አኳያ በጎ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው” ብለዋል፡፡

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን በማስጠበቅ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝም ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን በመጠቀም ዘርፈ ብዙ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን በማንሳት፡፡

በበዓሉ ላይ ከተገኙት መካከል ወይዘሮ አስቴር ሳርበ እንደገለፁት እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የፌዴራሊዝም ስርዓቱን ማጠናከር ይገባል፡፡ 

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ፣ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዴላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች ከአጎራባች ክልሎች የተጋበዙ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም