ቀጥታ፡

ባለድርሻ አካላት አካል ጉዳተኞችን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር በመዘርጋት ቁርጠኝነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል-ሚኒስቴሩ

ሀዋሳ ፤ህዳር 23/2ዐ17 (ኢዜአ)--ባለድርሻ አካላት አካል ጉዳተኞችን የሚያሳትፍና በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር በመዘርጋት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

32ኛው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በብሔራዊ ደረጃ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ዛሬ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ኩነቶች ተከብሯል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ የዘንድሮ በዓል የሚከበረው "የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

ለመሪ ሀሳቡ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻልም የአካል ጉዳተኞችን የእኩል ዕድል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በመሆኑም በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት አካል ጉዳተኞችን የሚያሳትፍና በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር በመዘርጋት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

"አካል ጉዳተኞች ያላቸውን የአመራር ሚና ማሳደግ የእኛ ኃላፊነት ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚህ ላይ አበክረን እንሰራለን ብለዋል።

እስካሁን ሚኒስቴሩ የአካል ጉዳተኛ ዜጎች መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፣ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን መከበሩ የወጡ ድንጋጌዎችን ለማስተዋወቅና የህብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየር ገንቢ ሚና አለው ብለዋል።

አካል ጉዳተኞችን ለመሚለከቱ ጉዳዮች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል። 

የበዓሉ መከበር አካል ጉዳተኞች ክብራቸው፣ መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ አካታች ማህበረሰብ ለመፍጠር ፋይዳ እንዳለውም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የበዓሉ መከበር የአካል ጉዳተኞችን ድምጽ ከፍ አድርጎ ለማሰማት ያግዛል።


 

እንዲሁም በሁለንተናዊ መልኩ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር፣ የአመራር ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግና ለአካል ጉዳተኞች ተገቢ ድጋፍ እንዲሰጥ ለማሳሰብ መሆኑንም አስታውቀዋል።

"የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ብቻ የሚተው ሀላፊነት ባለመሆኑ ሁሉም ከጎናቸው ሊቆም ይገባል" ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ  እመቤት ኢሳያስ ናቸው።


 

በክልሉ የአካል ጉዳተኞች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በክልሉ መንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዓሉን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን እና የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን ከፓናል ውይይት በተጨማሪ በአውደ ርዕይ፣ በደም ልገሳ እና መሰል ኩነቶች ተከብሯል።

በዓሉ በብሔራዊ ደረጃ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ሲከበር የሁሉም ክልሎች የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ፕሬዚዳንቶችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም