የደን አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫው ኢትዮጵያ የደን ምርቷን ለዓለም ገበያ በስፋት ማቅረብ የሚያስችላት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደን አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫው ኢትዮጵያ የደን ምርቷን ለዓለም ገበያ በስፋት ማቅረብ የሚያስችላት ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ጊዜያዊ የደን አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ማግኘቷ የደን ልማት ምርቷን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም የሚያሳድግ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለጸ፡፡
የደን አስተዳደር ምክር ቤት የኢትዮጵያን የደን አስተዳደር ስታንዳርድ ማጽደቁን ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል፡፡
የደን አስተዳደር ምክር ቤት የደን ልማት አስተዳደርን በማሳደግ ምርታማና ምቹ ዓለምን ለመፍጠር እ.አ.አ በ1993 የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡
በዚህም ዓለም ላይ ከ150 ሚሊየን ሄክታር በላይ የምስክር ወረቀት የተሰጠው የደን መሬት ያስተዳድራል፡፡
የደን አስተዳደር ስታንዳርድ የኢትዮጵያን የደን ልማት ዘርፍ በማጠናከር ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የደን ልማት ምርቶችን ጥራትና ተፈላጊነት ያሳድጋል ተብሏል።
በተለይም የሥነ ምህዳር ተጽፅኖን ለመቀነስ እንደ ዉሀ፣ ካርበን፣ ብዝሀ ህይወት እና መሰል ዘርፎችን ለመጠበቅ ያግዛል።
ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የመሰለፍ እቅዷን እውን ለማድረግ በ2025 ዓ.ም 15 ሚሊየን ሄክታር የተራቆተ መሬት በደን ለመሸፈን እየሰራች ነው።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም፤ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም፣ ለኢኮኖሚና ለደን መስፋፋት የጎላ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የደን ልማት አስተዳደር ደረጃው የተጠናከረ የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት የደን ጭፍጨፋን ማስቀረት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተጠናከረ የደን ልማት አስተዳደር እና ቁጥጥር ስርዓትን በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የደን ጥበቃ ከማጠናከር ባለፈ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የደን ልማት ምርቶችን በጥራትና በብዛት ማቅረብ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ በብዛት የሚመረቱ የቀርከሃ ምርቶችን በተሻለ ጥራትና ተወዳዳሪነት ወደ ዓለም ገበያ ለማውጣት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ፤ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የደን አስተዳደር ደረጃ ስር መካተቷ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የደን አስተዳደር ደረጃ መፅደቁ ኢትዮጵያ እና የደን አስተዳደር ምክር ቤቱ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ትብብር እና የጋራ ራዕይ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የደን አስተዳደር ምክር ቤቱ ለአስተዳደር ደረጃው ገቢራዊነት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የደን አስተዳደር ማረጋገጫ ካገኙ 85 ሀገራት አንዷ መሆኗን የገለጹት አስተባባሪዋ፤ አሰራሩ እስከሚሻሻል ወይም እስከሚቀየር ድረስ የአስተዳደር ስታንዳርዱን መጠቀም ትችላለች ብለዋል፡፡