ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ሰቆጣ ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፡-  በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር መስራት እንደሚገባ የዞኑ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አስገነዘቡ።  
በአስተዳደሩ "አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሀሳብ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሰቆጣ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል። 

ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ሃይሉ ግርማይ እንደገለፁት፤ በብሄረሰብ አስተዳደሩ አካል ጉዳተኞችን የማሳተፍና ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአስተዳደሩ በሚፈጠሩ የስራ እድሎችና ሌሎች ኢኮኖሚየዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጡ ዘርፎች የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ አካታች እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በቀጣይም በዞኑ የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ትበርህ ታደሰ በበኩላቸው፤ የአካል ጉዳተኞች ቀን በትምህርት ቤቶች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከበር ቆይቷል።

መምሪያው የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከባላድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ የስራ ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በዚህም በርካታ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

''የአካል ጉዳተኞች ቀን መከበር የተዛቡ አመለካከቶች እንዲታረሙ የሚያግዝ ነው'' ያሉት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ሰብሰቢ አቶ ኪሮስ ቸኮለ ናቸው። 

በሀገራችን የአካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ የዓለም አቀፍ ህግጋትን ተቀብላ ወደ ተግባር መገባቷን ገልፀው፤ ለአካል ጉዳተኞች የተሰጠው ትኩረት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። 

አካል ጉዳተኞች ያሳተፈ ልማት እንዲከናወን በየደረጃው ያሉ አስፈፃሚዎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። 

በበዓሉ ላይ የአስተዳደሩ የስራ ሀላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም