ቀጥታ፡

በባሕር ዛፍ የተሸፈነ ማሳቸውን በፍራፍሬ ልማት በመተካት የተለወጡ የከምባታ ዞን አርሶ አደሮች

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን ሀደሮ ጡንጦ ወረዳ ነዋሪ ናቸው አቶ ወንድሙ ሱጋሞ።

የአርሶ አደር ወንድሙ ሰፈር እና ጓሮ በአትክልትና ፍራፍሬ የተዋበ ሲሆን አረንጓዴ ማሳቸው ከውበት ባሻገር ሌማታቸውንም፣ ኪሳቸውንም እንዲሞሉ አስችሏቸዋል።

አቶ ወንድሙ በክልሉ ግብርና ቢሮ የባሕር ዛፍ ማሳዎችን ወደ አትክልትና ፍራፍሬ የመለወጥ ንቅናቄን በመከተል ለረዥም ዓመታት በባሕር ዛፍ የተሸፈነ ማሳቸውን በፍራፍሬ ልማት ተክተዋል።

ለሽያጭ ብቁ ለመሆን ከአሥር ዓመታት ያላነሰ ጊዜ የሚወስደውን ባሕር ዛፍ በመመንጠር ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ላይ የተከሏቸው የሙዝ ችግኞች አሁን ላይ ለፍሬ እየደረሱ መሆኑን ይናገራሉ።


 

በግብርና ባለሙያዎች አነሳሽነት በሙዝና አቮካዶ ተክል የሸፈኑት ማሳቸው ላይ የተመለከቱት ውጤት ደግሞ "ለምን ዘገየሁ?'' የሚል ቁጭት እንዲያድርባቸው አድርጓል።

በተመሳሳይ በሀደሮ ጡንጦ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አቶ ለገሰ ደነሞ፤ ከ8 ሄክታር በላይ መሬታቸው በባሕር ዛፍ ተሸፍኖ መቆየቱን ይናገራሉ።


 

አሁን ግን ለሙከራ ያህል 2 ሄክታር መሬት ላይ ያለ ባሕር ዛፍን በማስወገድ ዝንጅብል እያለሙበት ሲሆን በሰባት ወራት ውስጥ ምርት እያገኙ ነው።

በ1 ሄክታር የዝንጅብል ሰብል እስከ ግማሽ ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገቢ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ለገሰ፤ ባሕር ዛፍ ቢሆን ግን አሥር ዓመት ቆይቶ ይህን ያህል ገቢ እንደማያስገኝ ልዩነቱን ያብራራሉ።


 

በቀጣይም በባሕር ዛፍ የተሸፈነ ቀሪ ማሳቸውን ወደ ፍራፍሬ፣ ቅመማቅመምና የስራስር ልማት ለመለወጥ ተዘጋጅተዋል።

አቶ ወንድሙ እና አቶ ለገሰ ከራሳቸው አልፈው ባሕር ዛፍን ለምግብነት በሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬ የመለወጥ አስተሳሰብ እንዲሰርፅ በማድረግ በአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ላይ በጎ መነሳሳትን ፈጥረዋል።

የእነርሱን አርዓያነት የወሰዱ አርሶ አደሮችም አሁን ላይ መጠቀም እንደጀመሩ በማውሳት፤ እስከዛሬ በአመለካከት ችግር ይህን ዕድል ባለመጠቀማቸው ተቆጭተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዑስማን ሱሩር እንደሚሉት፤ በክልሉ የ30-40-30 ኢኒሼቲቭ አንዱ ትኩረት በባሕር ዛፍ የተሸፈኑ መሬቶችን ለምግብነት በሚውሉ ተክሎች መሸፈን ነው።


 

ይህም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገቢ እንዲሁም ለወጪ ንግድ የሚውሉ ምርቶችን በማልማት ረገድ ጥሩ ውጤት እየታየበት ነው ብለዋል።

ዓላማውም የተቀናጀ ግብርናን በመተግበር የአርሶ አደሮችን ሕይወት ማሻሻልና ከድህነት ወደ ብልፅግና ማሸጋገር መሆኑን አንስተዋል።

በከምባታ ዞን አብዛኛው ማሳዎች በባሕር ዛፍ እንደተሸፈኑ ያነሱት አቶ ዑስማን፤ ይህን የባከነ ዕድል ለማካካስ የተጀመረው ንቅናቄ የአርሶ አደሮችን አመለካከትና ኑሮ እየለወጠ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም