ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ጠንካራ ተቋማትን ገንብታለች-የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ጠንካራ ተቋማትን ገንብታለች-የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካን የአቪየሽን ዘርፍ እንድትመራ ያስቻሉ ጠንካራ ተቋማትን መገንባቷን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተመሰረተበትና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማቋቋሚያ ስምምነት የተፈረመበት 80ኛ ዓመት በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በሚካሄደው የበዓሉ አከባበር የፓናል ውይይት፣ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።
ፖቴዝ_25 የተሰኘችው አውሮፕላን እ.አ.አ. በ1929 ከጅቡቲ ተነስታ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አየር ላይ በመንሳፈፍ ገፈርሳ አካባቢ ስታርፍ የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ እንደተጀመረ ታሪክ ይናገራል።
እ.አ.አ. በታህሳስ 7 ቀን 1944፤ በአሜሪካ ቺካጎ ከተማ በተካሄደ ጉባኤ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ሲቋቋም አፍሪካን ወክለው ከተገኙ ሶስት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መመስረትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በተለያዩ ጊዜያት በወጡ የማቋቋሚያ ህጎች አደረጃጀትና ኃላፊነቱን ሲያሻሽል ቆይቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያስመዘገባቸው ካሉ ስኬቶች ጀርባ ጠንካራ ደጀን የሆነው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ ተናግረዋል።
በአገሪቱ ጠንካራ የሲቪል አቪዬሽን ተቋም መኖሩ ጠንካራና ስመ ጥር አየር መንገድ እንዲኖረን አድርጓል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በቀዳሚነት የምትመራ ሀገር እንድትሆን ማስቻሉንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከበርካታ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የአየር ትራንስፖርት ስምምነት መፈራረሙን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፋዊ መዳረሻዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ጠቅሰዋል።
ባለስልጣኑ የኤርፖርቶች ግንባታና ቁጥጥር ሂደትን የማስተዳደር ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ባለፉት ዓመታት ባካሄደው ለውጥ የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች 23 የደረሱ ሲሆን አራቱ ዓለም አቀፍ ደረጃን ማሟላታቸውን ጠቅሰዋል።
አውሮፕላኖችን በመመዝገብ ደህንነታቸውን የማረጋገጥ፣ ለአብራሪዎች፣ ለቴክኒሻኖችና ለአስተናጋጆች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት የመስጠት፣ የማሠልጠኛና የጥገና ተቋማትን ፈቃድ እና ሌሎች ተግባራትን በብቃት እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉ ላይ በወሳኝና አንገብጋቢ የዓለም የአቪየሽን ዘርፍ ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በርካታ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2035 በአፍሪካ ተመራጭና ግንባር ቀደም የአቪዬሽን ማዕከል ለመሆን ብሔራዊ የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።