ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር የብዝሃነት እና አንድነት ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ አድርጓል - አፈ ጉባኤ አስካል አልቦሮ

አሶሳ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፦የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር ብዝሃነት እና አንድነት ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ ማድረጉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስካል አልቦሮ ተናገሩ።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ማጠቃለያ መርሃ ግብር በቢኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደረጃ  በአሶሳ ከተማ በሲምፖዚየም ተከብሯል።

በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ አስካል እንደተናገሩት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር በሀገሪቷ ያለውን ብዝሃነት እና አንድነት ሚዛን እንዲጠብቅ አድርጓል።


 

የሀገሪቷ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እውቅና የሰጠ ነው" ያሉት አፈ ጉባዔዋ፤ ቀኑ የተዛቡ ትርክቶችን በማረም ረገድ አዎንታዊ ሚና አለው ብለዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን  ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እና ሀገራዊ መግባባት እንዲጎለብት በማድረግ በኩልም ተጨባጭ ለውጥ የታየበት ነው ብለዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው ክልሉ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቀኑ መከበርም አብሮነትን ለማጠናክር ያግዛል ብለዋል።

ቀኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በአንድነት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ቃል የሚያድሱበት እና ብዝሃነታቸው ጉልበት መሆኑን የሚያሳዩበት ቀን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ቀኑ በክልሉ በስፖርታዊ ውድድሮችና በሌሎች መርሃ ግብሮች ሲከበር የቆየ ሲሆን፤ አሸናፊ ለሆኑ ስፖርተኞችም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በፕሮግራሙ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድርን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን  በክልሉ ደረጃ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ነገ በኡራ ወረዳ በአደባባይ እንደሚከበር ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም