ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎችን ለማጠናከርና ምርታማነትን በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ የአመራሩን አቅም ማጎልበት ይገባል-ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

ጋምቤላ፤ ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፦ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎችን ለማጠናከርና ምርታማነትን በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ የአመራሩን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ማጎልበት ይገባል ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለፁ። 

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጋምቤላ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመተባበር በፕብሊክ ኢንተርፕርነርሺፕና ኢኖቬሽን ስነ-ምህዳር ግንባታ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ያዘጋጀው አውደጥናት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል። 

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት መንግስት በመላ ሀገሪቱ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። 

የእውደጥናቱ ዋና ዓላማም በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ልማቱን ስኬታማ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። 

ክልሉ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለማዕድንና ለቱሪዝም ልማት ያለውን ሰፊ አቅም በመጠቀም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአመራሩ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። 

ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎችን ለማጠናከርና ምርታማነትን በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ የአመራሩን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴሩ የአመራሩን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት እና ለኢንተርፕርነርሺፕና ለኢኖቬሽን ስነ ምህዳር ግንባታ የጀመራቸውን የድጋፍና የክትትል ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። 


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራባቸው ካሉ መካከል ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር አንዱ ነው። 

በተለይ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ሴቶችንና ወጣቶችን ያሳተፈ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩ ሥራ ፈጣሪዎችን ቁጥር ከማሳደግ ባለፈ ለሌሎች ዜግችም የሥራ እድል የሚፈጥሩበት ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። 

አውደጥናቱ የሥራ ዕድል ፈጠራው በአካባቢያዊ የተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሠሰረተ እንዲሆንና ዜጎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ የአመራሩን ሚና የሚያጎለብት መሆኑን አስረድተዋል። 


 

የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሯች በየክ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ በክልሉ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። 

በዛሬው ዕለት ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እየተሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ አውደጥናት ይህንኑ ተግባር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል። 

አውደጥናቱ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጋምቤላ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ የጋራ በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም