የመቻል ስፖርተኞች የኢትዮጵያ ስፖርት ክለቦች ተምሳሌት መሆን አለባችሁ-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የመቻል ስፖርተኞች የኢትዮጵያ ስፖርት ክለቦች ተምሳሌት መሆን አለባችሁ-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፦መቻል ስፖርተኞች የኢትዮጵያ ስፖርት ክለቦች ተምሳሌት መሆን አለባችሁ ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥በናይጄሪያ አቡጃ በተካሄደው ሁለተኛው የመላው አፍሪካ የጦር ኃይሎች ስፖርት ፌስቲቫል ለተሳተፈው የመቻል ስፖርት ክለብ ልዑካን ቡድን አቀባበል አድርገዋል።
መቻል ስፖርት ክለብ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሞዴል ነው፤ ብዙ ታሪክ ያለው የአንጋፋ ስፖርተኞች መፍለቂያ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፥ ግዙፍ ክለብ መሆኑን ከተቋም አልፎ ሀገርን ባስጠሩ ስፖርተኞች ውጤት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የመቻል ስፖርተኞች በስፖርቱ ዘርፍ ከተቋም ባለፈ የኢትዮጵያ አደራ እንዳለባቸው የገለፁት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፥ ከዓመታት በፊት ከደረጃው ወርዶ የነበረውን አንጋፋውን መቻል የስፖርት ክለብ ለመመለስ በርካታ ሥራዎች በትኩረት መከናወናቸውን አመልክተዋል።
የክለቡን የቦርድ አመራር በመቀየር በአዲስ አደረጃጀት ማዋቀር፣ ለስፖርት ክፍሉ አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉ ማሟላት፣በኢኮኖሚ ምክንያት ክፍተት እንዳይፈጠር ቀድሞ በጀት በመመደብ መቻልን ወደተፈለገው አቅጣጫ ማምጣት እየተቻለ ነው ብለዋል።
በቀጣይም እንደ ተቋም ማድረግ የሚገባንን ሁሉ በመሥራት ኢትዮጵያን የሚመጥን በመልካም ዲስፕሊን የተገነባ ለሌላው ክለብ አርአያ መሆን የሚችል የስፖርት ቤተሰብ መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ከመቻል ስፖርተኞች ብቃቱ የተረጋገጠ በሁሉም ዲስፕሊን የተቀረፀ ሰው ያስፈልጋታል፣ ለዚህም የመቻል ስፖርተኞች መበርታት አለባችሁ ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ።
መቻል በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመቻል ስፖርተኞች የኢትዮጵያ ስፖርት ክለቦች ተምሳሌት መሆን አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሥነ ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን አጠቃላይ የውድድሩን ሪፖርት ለጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አቅርበዋል።
መቻል በናይጄሪያ አቡጃ በተካሄደው ሁለተኛው የመላው አፍሪካ የጦር ኃይሎች ስፖርት ፌስቲቫል ሰባት ወርቅ ስምንት ብር ሁለት ነሐስ በድምሩ 17 ሜዳሊያዎች እና 10 ዲፕሎማ ማግኘቱን ገልጸዋል።
መቻል በፌስቲቫሉ በአጠቃላይ ስፖርተኞች አምስተኛ፣ በአትሌቲክስ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቀቁን ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በፌስቲቫሉ ላይ ከ25 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።