ቀጥታ፡

 የደን አስተዳደር ምክር ቤት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ማግኘቷን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ህዳር 23/2017(ኢዜአ)፦  የደን አስተዳደር ምክር ቤት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ የደን ልማት አስተዳደር ደረጃ ማረጋገጫ ማግኘቷን ይፋ አደረገ።

የደን አስተዳደር ምክር ቤት የደን ልማት አስተዳደርን በማሳደግ ምርታማና ምቹ ዓለምን ለመፍጠር እንደ እ.አ.አ በ1993 የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው።

ተቋሙ  ከ150 ሚሊየን ሄክታር በላይ የምስክር ወረቀት የተሰጠው የደን መሬትንም ያስተዳድራል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የደን አስተዳደር ስታንዳርድ የኢትዮጵያን የደን ልማት ዘርፍ በማጠናከር ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የደን ልማት ምርቶችን ጥራትና ተፈላጊነት ያሳድጋል ተብሏል።

በተለይም የሥነ ምህዳር ተጽፅኖን ለመቀነስ እንደ ዉሀ፣ ካርበን፣ ብዝሀ ህይወት እና መሰል ዘርፎችን ለመጠበቅ ያግዛል።

ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የመሰለፍ እቅዷን እውን ለማድረግ በ2025 ዓ.ም 15 ሚሊየን ሄክታር የተራቆተ መሬት በደን ለመሸፈን እየሰራች ነው።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም፤ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

የደን ልማት አስተዳደር ደረጃው የተጠናከረ የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት የደን ጭፍጨፋን ማጥፋት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተጠናከረ የደን ልማት አስተዳደር እና ቁጥጥር ስርዓትን በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የደን ጥበቃ ከማጠናከር ባለፈ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ የደን ልማት ምርቶችን በጥራትና በብዛት ማቅረብ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ በብዛት የሚመረቱ የቀርከሃ ምርቶችን በተሻለ ጥራትና ተወዳዳሪነት ወደ ዓለም ገበያ ለማውጣት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

የደን አስተዳደር ምክር ቤት የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አናህ አጋሻ፤ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የደን አስተዳደር ደረጃ ስር መካተቷ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የደን አስተዳደር ደረጃ መፅደቁ ኢትዮጵያ እና የደን አስተዳደር ምክር ቤቱ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ትብብር እና የጋራ ራዕይ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የደን አስተዳደር ምክር ቤቱ ለአስተዳደር ደረጃው ገቢራዊነት  ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም