በአፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫል አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው መቻል አዲስ አበባ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫል አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው መቻል አዲስ አበባ ገባ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2017 (ኢዜአ)፦ በናይጄሪያ አቡጃ ከተማ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫል በአጠቃላይ ውድድሮች አምስተኛ፣ በአትሌቲክስ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ደረጃን የመቻል ስፖርት ክለብ አዲስ አበባ ገብቷል።
የክለቡ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድ አቀባበል አድርገውለታል።
የስፖርት ፌስቲቫሉ ከህዳር 9 እስከ 21 ቀን 2017 ዓ.ም በአቡጃ መካሄዱን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአትሌቲክስ ዘርፍ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው መቻል በሰባት ወርቅ በስምንት ብር በሁለት ነሐስ አጠቃላይ በ17 ሜዳሊያዎች ከኬንያ በመቀጠል በአትሌቲክስ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ በአጠቃላይ ውጤት የአምስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን አጠናቋል።
በፌስቲቫሉ ላይ ከ25 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።