ቀጥታ፡

በክልሉ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ለመግታት የተጠናከረ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ጠንክረን ልንሰራ ይገባል

ጋምቤላ ህዳር 23/2017 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭት ለመግታት የተጠናከረ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር  ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

37ኛው የዓለም ኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን "ሰብዓዊ መብትን ያከበረ የኤች አይ ቪ አገልግሎት ለሁሉም’’ በሚል መሪ ሐሳብ  ዛሬ በጋምቤላ ክልል ደረጃ በጋምቤላ ከተማ ታስቦ ውሏል።

ርዕሰ መስተዳድሯ በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የኤች አይ ቪ /ኤድስ  እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር አመራሩ ጠንካራ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል።

በሽታው በተለይም አምራቹን ኃይል የሚጎዳ በመሆኑ በክልሉ ቀጣይ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።


 

በመሆኑም በክልሉ የበሽታውን የስርጭት መጠን  ለመግታት በየደረጃው የሚገኘው የአመራር አካላት የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ተግተን ልንሰራ ይገባል ነው ያሉት።

እንዲሁም ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ወገኖች አስፈላጊውን የፀረ-ኤች አይ ቪ/ኤድስ የህክምና አገልግሎትና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ጭምር አመራሩ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የኤች አይ ቪ/ኤድስን ቀን በክልሉ በልዩ ትኩረት ማክበር ያስፈለገው የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በሽታውን የመከላከሉን ስራ ይበልጥ ለማጠናከር በማለም መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሯ ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ በበኩላቸው የኤች አይ ቪ ቫይረሱ ስርጭትን ለማግታት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በሽታውን ለመከላከል በተከናወኑት ስራዎች በክልሉ የበሽታው ስርጭት መጠን የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል ያሉት ኃላፊው፤ ሆኖም የክልሉ የበሽታው የስርጭት መጠን  አሁንም ጠንካራ ሥራ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው ብለዋል።

በመሆኑም የበሽታውን ስርጭት የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ በጤና ተቋማት ብቻ ውጤታማ ስለማይሆን ሁሉም ማህበረሰብ እና ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት እንዲሰሩ ኃላፊው ጠይቀዋል።

አሁን ላይ የክልሉ የኤች አይ ቪ/ኤድስ የስርጭት መጠን 3 ነጥብ 24 መሆኑንና ይህም ከሀገር አቀፉ የስርጭት መጠን በ2 ነጥብ 37 ብልጫ ያለው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዴንግ ናቸው።


 

ስለሆነም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ሁሉም ተቋማት የኤች አይ ቪ/ኤድስን ስርጭት የመከላከሉን ስራ ከመደበኛው ስራው ጋር አካቶ በመስራት እንዲያግዛቸው አስገንዝበዋል።

በተለይም በፈረንጆች አቆጣጠር በ2030 የኤች አይ ቪ/ኤድስ በሽታን የማህረሰቡ የጤና ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ለተያዘው ግብ መሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ድራማዎች የተካሄዱ ሲሆን፤ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የምክርና የደም ምርመራ አገልግሎት ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም