ቀጥታ፡

መንግስት ወደ ሰላም የተመለሱ ታጣቂዎችን እንዲቋቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል -ብርጋዲየር ጄኔራል አብደላ መሃመድ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2017 (ኢዜአ) ፦መንግስት ወደ ሰላም የተመለሱ ታጣቂዎችን እንዲቋቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የምዕራብ ጎንደር ዞን የፀጥታ ምክር ቤት አስተባባሪ ብርጋዲየር ጄኔራል አብደላ መሃመድ ገለጹ።

መንግስት የታጠቁ ሀይሎች ትጥቅ በመፍታት ወደ ሠላማዊ ሁኔታ እንዱመለሱና ጥያቄዎች በውይይት እንዲፈቱ በተከታታይ እያደረገ ባለው ጥሪና ጥረት አማካኝነት ራሱን "የቅማንት ታጣቂ ቡድን" ብሎ የሚጠራው ኃይል የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሰላማዊ መንገድ ገብቷል።


 

በዚህም መቃ ቀጠና የሚንቀሳቀሰው ራሱን "የቅማንት ታጣቂ ቡድን" ብሎ የሚጠራው ኃይል በሀገር ሽማግሌዎች አገናኝነት በተደረገው ውይይት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ በምህረት ለመግባት መስማማታቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የፀጥታ ምክር ቤት አሥተባባሪ ብርጋዲየር ጄኔራል አብደላ መሃመድ ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ ከሕዝባቸው ጋር በመቀላቀል ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከቀበሌ መሪዎች እና ከመንግሥት አካላት ጋር አብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።


 

በቀጣይም በስራቸው ያሉ እስከ 250 የሚደርሱ አባሎቻቸውን ይዘው መንግሥት በሚሰጣቸው አቅጣጫ መሠረት የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንደሚመለሱ መግባባት ላይ መደረሱን ብርጋዲየር ጄኔራል አብደላ ተናግረዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ወደ ሰላም የተመለሱ ታጣቂዎችን በመንግሥት በኩል እንዲቋቋሙ የሚደረገውን ጥረት በልዩ ልዩ መንገድ ለመደገፍ እንደሚሠራም አመልክተዋል።

በቀበሌው የሚከናወኑ የመንግሥት ተግባራት ከምን ጊዜውም በላይ እንዲሳለጡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

በውይይቱ ላይ የምዕራብ ጎንደር ዞን የጸጥታ ምክር ቤት አስተባባሪ ጄኔራል አብደላ መሐመድ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እያሱ ይላቅ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢ እና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደግነት አበበ፤ የመተማ ወረዳ መሪዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የታጣቂ ተወካዮች መገኘታቸውን ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሰላም ስምምነት ትናንት መፈራረማቸው ይታወቃል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራር የነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ነው ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት የሰላም ስምምነቱን የተፈራረሙት።

በቅርቡም የአፋር ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታጣቂዎች ‘ትጥቃቸውን ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በማስረከብ ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን አክብረን በሠላማዊ መንገድ ህዝባችንን ለማገልገል በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ማለታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም