ቀጥታ፡

መቄዶንያ የሰው ልጆች ያለምንም የሀይማኖት፣የዘር፣የቀለም ልዩነት የሚደገፉበት ማዕከል ነው

አዲስ አበባ፤ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦መቄዶንያ የሰው ልጆች ያለምንም የሀይማኖት፣የዘር ፣የቀለም ልዩነት የሚደገፉበት ማዕከል መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር የፀሎት መርኃ ግብር አካሂዷል።

በመርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለን ጨምሮ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።


 

''ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው'' በሚል መርህ የተመሰረተው መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በእርጅና ዘመን ጧሪ ያጡትን፣ በከፍተኛ ህመም የሚሰቃዩና ረዳት የሌላቸው ወገኖችንና የአዕምሮ ህሙማንን መንከባከብ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚሁ ወቅት፥ሰላም የመግባባት፤ የመተማመን እና በሰላም የመንቀሳቀስ መሰረት ነው በማለት ተናግረዋል።

ሰላም ለሰው ልጅ ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሁሉም ከጥላቻ፣ ከቂም፣ከጦርነትና ከበቀል መራቅ አለበት ብለዋል።

ሰላም ከሌለ ተስፋ አለመኖሩን ገልፀው፥ ተስፋ፣ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቀዳሚነት ሰላም ያስፈልጋል በማለት አክለዋል።

በሀገራችን ሰላም ሰፍኖ የሚጠበቀው አንድነትና ዕድገት እንዲመጣ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘርና ሀይማኖት ሳይገድበው በአንድነት ለሰላም መቆም አለበት ብለዋል።


 

የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራች ቢንያም በለጠ በበኩላቸው፥ ማዕከሉ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ 44 ቅርንጫፎቹ ከ 8 ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን እየረዳ ይገኛል።

በቀጣይም ቅርንጫፎቹን ወደ 240 ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

መቄዶንያ ማለት ትንሿ ኢትዮጵያነች ያሉት አቶ ቢኒያም፥የሀይማኖት ፣ የዘር፣የቀለም ልዩነት ሳይኖር ሁሉም የሚደገፉበት ነው ብለዋል።

ማዕከሉ የምግብና መጠለያ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሃይማኖት ተቋማትም መንፈሳዊ ትምህርት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ፕሮግራሙን በማዘጋጀትና የማዕከሉን የስራ እንቅስቃሴ በመጎብኘቱ አመስግነዋል።

መቄዶንያ ለመረዳት በሚደረገው ተግባር ውስጥ ሁሉም ድጋፉን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በዚህም በአጭር የጽሑፍ መልዕክት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት በሆነው 8161 አማካኝነት ድጋፍ አንዲያደርጉ ነው መልዕክት ያስተላለፉት።

የእምነት አባቶቹ መርኃ ግብሩ የተከናወነው ለሃገር ሰላምና መረጋጋት ለመፀለይና በተለያዩ ምክንያት ችግር ውስጥ ከወደቁ ወገኖች ጎን መሆናችንን ለማሳየት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም