ቀጥታ፡

በሀገሪቱ ጤናማ የግብይት ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ ነው --ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) 

ደሴ፤ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦በሀገሪቱ ጤናማ የግብይት ስርዓትን በመፍጠር የኢትዮጵያን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ እንደሚገኝ  የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኮምቦልቻ ከተማ በ85 ሚሊዮን ብር ያስገነባው ዘመናዊ የምርት ማከማቻ መጋዘን ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርጓል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ካሳሁን ጎፌ እንደገለፁት፤ ጤናማ የግብይት ሰንሰለትና ስርዓትን በመፍጠር የኢትዮጵያን ገቢ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከወጪ ንግድ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተተገበረ ሲሆን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተደረገ እንቅስቃሴ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል። 

በተለይ ህገወጥ ንግድንና ህገወጥ ኬላዎችን በመከላከል ምርት በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲችልና ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የተለዩ 283 ህገወጥ ኬላዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የተሳለጠ የግብይት ስርዓት እንዲኖር መስተካከል ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምገኘሁ ነገራ በበኩላቸው፤ የተሻሻለ የምርት ግብይት ስርዓትን በመፍጠር ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ዘመናዊ የምርት ማከማቻ መጋዘንና የማገበያያ ማዕከላት እየተመቻቹ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ በ85 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ለአገልግሎት የተዘጋጀው መጋዘን የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ መጋዘኑ ከ150 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት የመያዝ አቅም እንዳለው ገልፀዋል።

መጋዘኑ በውስጡ ዘመናዊ ሚዛን፣ አገልግሎት መስጫ ቢሮዎችና ሌሎችንም ያካተተ እንደሆነ ተናግረዋል።

ምርት አቅራቢዎችና አርሶ አደሮች ምርታቸውን በጥራት ከማስቀመጥና ከመገበያየት ባለፈ ወቅታዊና ታማኝ መረጃ እንዲደርሳቸውም ያደርጋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።


 

ዛሬ የተመረቀው የምርት ማከማቻ መጋዘን ምርት በጥራት ወደ ገበያ ለማድረስ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በክልሉ ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የኤክስፖርት ምርት ለማቅረብም ምርቱ በጥራት እንዲሰበሰብ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት በማሰብ በስምንት ከተሞች በ450 ሚሊዮን ብር ወጪ የገበያ ማዕከላትን ለመገንባት ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

እነዚህና መሰል ተግባራትን በውጤታማነት ለማከናወን ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም የመጠበቅ ሚናውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም