ኤች አይቪ ኤድስ የማህበረሰብ የጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኤች አይቪ ኤድስ የማህበረሰብ የጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታትና በ2030 በአገሪቱ የማህበረሰብ የጤና ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ በማተኮር በትብብር መስራት እንደሚሰራ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት እያከናወነችው ያለው ስራ በ2030 ኤች አይቪ የማህበረሰብ የጤና ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት በአለም ላይ 40 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች የኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝና ከነዚህ መካከል 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑት በ2023 በቫይረሱ መያዛቸውን የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
የአለም የኤድስ ቀንን በተመለከተ በተዘጋጀ መድረክ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንዳሉት አፍሪካ ለኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትና ሞት ከፍተኛ ተጋላጭ በመሆኗ በትኩረት መስራትን ይጠይቃል።
በኢትዮጵያ የኤች አይቪ ኤድስን ስርጭት ለመቆጣጠርና ለመከላከል የተሰራው ስራ ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀው በዚህም የኤች አይቪ አድስ ስርጭት ከሁለት አመት በፊት 0 ነጥብ 9 በመቶ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ምጣኔውን ወደ 0 ነጥብ 8 በመቶ መቀነስ መቻሉን አንስተዋል።
ሆኖም በስድስት ክልሎች ያለው ስርጭት በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ በመሆኑ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎችና የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በ2025 የ95-95-95 በመቶ የምርምራ፣ የሕክምናና የቫይረሶችን መጠን ከሰውነት የመቀነስ እቅድ በማሳካት ረገድ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗንና ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
እኤአ በ2030 ኤች አይ ቪ/ኤድስ የማህበረሰብ ጤና ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስና የኤች አይቪ ስርጭትና ሞት ምጣኔን ለመቀነስ እያደረገች ያለውን ጥረት ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች አይቪ ኤድስ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክሪታያዋን ቦንቶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በ2030 ኤች አይ ቪ/ኤድስ የማህበረሰብ ጤና ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በትክክለኛው መስመር ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ተግባር በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን በመጠቆም።
ኢትዮጵያ የኤች አይቪ ስርጭትን ለመግታትና ለመቆጣጠር ለምታደርገው ጥረት የአሜሪካን መንግስትና ህዝብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁት ደግሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር አርቪን ማሲንጋ ናቸው።