ቀጥታ፡

ባለፉት አመታት በሀገራችን የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በንግግር እንጂ በአፈሙዝ እንደማይፈታ በተደጋጋሚ ታይቷል - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት አመታት በሀገራችን የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በንግግር እንጂ በአፈሙዝ እንደማይፈታ በተደጋጋሚ ታይቷል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ክንፍ ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ መካከል በዛሬው እለት የተፈረመው የሰላም ስምምነት እጅግ ሊበረታታ የሚገባውና እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ለምናደርገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።

እንደ ብልፅግና ፓርቲ ሰላም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተገንዝበን እራሳችንን ለንግግር፣ ለድርድር እና ለትብብር ክፍት አድርገናል ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።


 

ህብረተሰባችን በተደጋጋሚ የሚያቀርባቸው የህግ የበላይነት መከበር ጥያቄዎች በምሉዕነት እንዲመለሱ ለማድረግም የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ጥረቶችን ይበልጥ አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባ እናምናለን ብለዋል።

ባለፉት አመታት በሀገራችን የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት በንግግር እንጂ በአፈሙዝ ኃይል በዘላቂነት ሊፈታ እንደማይችል በተደጋጋሚ ታይቷል ሲሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም በየትኛውም የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ታጣቂዎች አሁንም ቢሆን የተሻለው አማራጭ ሰላማዊ መንገድ መሆኑን ተገንዝበው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ምርጫቸው እስካደረጉ ድረስ እንደ ብልፅግና ፓርቲ የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ መሆናችንንም ጭምር በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም