በኮምቦልቻ ከተማ የዘመናዊ ገበያ ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
በኮምቦልቻ ከተማ የዘመናዊ ገበያ ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
ኮምቦልቻ ፤ህዳር 22/2017 (ኢዜአ):-በኮምቦልቻ ከተማ የዘመናዊ ገበያ ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በስነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮናስ መላኩ ማዕከሉ አራት ዘመናዊ ሼዶች የተካተቱበት መሆኑንም ገልፀዋል።
የማዕከሉ መገንባትም የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በስፋት በማቅረብ የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ረገድ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በዚህም አምራቹና ሸማቹን በቀጥታ ከማገናኘት ባለፈ የጅምላ አከፋፋዮችም ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከ95 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚገነባ ሲሆን በአራት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
በተያያዘም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኮምቦልቻ ከተማ ያስገነባውን የምርት ማከማቻ መጋዘን ያስመርቃል ተብሎ ይጠበቃል።