የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራር የነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ነው ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት አዲስ አበባ ላይ በዛሬው ዕለት የሰላም ስምምነቱን የተፈራረሙት።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለመጡት ምስጋና አቅርበዋል።
ከጦረኞች በላይ ጦርነትን የሚያባብሱት ስለጦርነት የማያውቁ ናቸው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እኔ ካለኝ ልምድ አንፃር ጦርነት ጎጂ በመሆኑ የሰላምን መንገድ መርጣችሁ በመምጣታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ይህ አይነቱ ተግባር በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕስ መስተደድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የኦሮሞ ህዝብ በባህልና በወጉ መሰረት በሮቹን ጠምዶና ፈረሶችን ጭኖ በመውጣት ሰላም ይውረድ ባለው መሰረት ጥሪውን ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ በራሴና በክልሉ መንግስት ስም አመሠግናለሁ ብለዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ የመከላከያ ሠራዊቱ ለሰላም ስምምነቱ ላበረከተው አስተዋፅኦም ምስጋና አቅርበዋል።
በዚህ ዓለም የሰው ልጅ የፖለቲካ ልዩነት ያለው መሆኑን ያወሱት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ እኛም ያለንን የፖለቲካ ልዩነት በጠመንጃ ከመፍታት በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ወስነን ነው ስምምነቱን የመረጥነው ብለዋል።
ይህ ስምምነት ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
በመረሀ-ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጋዛሊ አባ ሲመል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር ሌተናል ጄነራል ዲሪባ መኮንን የኢትዮጵያ መከላከያ መረጃ አመራሮች አባገዳዎች ሀደ ሲንቄዎችና የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ አትሌቶች ተገኝተዋል።