19ኛውን የብሔር፤ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በተለያዩ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በድምቀት ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
19ኛውን የብሔር፤ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በተለያዩ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በድምቀት ተከበረ
አዲስ አበባ ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦19ኛውን የብሔር፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በደቡብ ኮሪያ እና ደቡብ ሱዳን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች ፣ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት እንዲሁም አጋር አካላት በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል፡፡
በሴኡል በተከበረው በዓል፥ በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የተለያዩ የብሔር፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚኖሩባት እና የብዙ እሴቶች መገኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም፥ በዓሉ ሕዝቦች እኩልነታቸውን፣ አንድነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን የሚያጠናክሩበት፥ ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያንፀባርቁበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የበለጠ ተቀራርበው እንዲተዋወቁና የጠነከረች አገር ለመገባት ሚናቸውን እንዲጫወቱም አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በበዓሉ የኢትዮጵያን ድንቅና ልዩ ልዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ቅርሶች ለኮሪያ ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ እና የሀገር ገፅታ ግንባታ የማሳደግ ተግባር ተከናውኗል፡፡
በተመሳሳይ በዓሉ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ፥ የሀገራችንን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የምናጠናክርበት እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነታችንን የምናጸናበት ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ የህዝቦች አንድነት እና ትጋት ለሀገር እድገት ትልቅ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸው፥ ሁሉም ዜጋ አንድነቱን ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባው መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከኤምባሲዎቹ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።