ቀጥታ፡

መቻል በአፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫል አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2017 (ኢዜአ)፦ የመቻል ስፖት ክለብ በናይጄሪያ አቡጃ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫል በአጠቃላይ ውድድሮች አምስተኛ፣ በአትሌቲክስ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ለስምንት ቀናት የተካሄደው ፌስቲቫል ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል። የመዝጊያ ስነ ስርዓትም ተካሄዷል።

በፌስቲቫሉ ላይ ከ25 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል።

ትናንት ከመዝጊያ ስነ ስርአቱ ቀደም ብሎ በተካሄደ የአራት አራት በመቶ ሜትር (4x400) የዱላ ቅብብል ኢትዮጵያ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። 

ኢትዮጵያን የወከለው የመቻል ስፖርት ክለብ በሰባት ወርቅ በስምንት ብር በሁለት ነሐስ አጠቃላይ በ17 ሜዳሊያዎች ከኬንያ በመቀጠል በአትሌቲክስ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ በአጠቃላይ ውጤት የአምስተኛ ደረጃን ይዞ  ውድድሩን አጠናቋል።

በመዝጊያ ስነ ስርአቱ ላይ የመቻል ስፖርት ክለብ ቡድን የሀገሪቱን ሰንደቅ አላማ ባነገቡት ጀግኖች አትሌቶቻችን እየተመራ በታዳሚዎች ፊት አልፏል።

የመከላከያ ሠራዊት የስነ ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደ ኪዳንና የመቻል ስፖርት ክለብ ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጀኔራል ኑሩ ሙዘይን እንዲሁም በናይጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለገሰ ገረመውና ሌሎች የኤምባሲው አባላት በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። 

በቀጣይ 3ተኛውን የመላው አፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫል ኢትዮጵያ ወይም ኢኳቶሪያል ጊኒ እንደሚያዘጋጁ የተገለጸ ሲሆን አዘጋጅ አገር በቀጣይ ይፋ ይደረጋል።

በፌስቲቫሉ ላይ የተሳተፈው የመቻል ስፖርት ክለብ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም