የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ለአገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው - አቶ አገኘው ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ለአገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው - አቶ አገኘው ተሻገር
ህዳር 22/2017 (ኢዜአ)፦ የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ለአገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘው ተሻገር ገለጹ።
19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአምቦ ከተማ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ሀጫሉ ካምፓስ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የዘንድሮው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል "አገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ በክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተሞች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል።
ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ እየተከበረ ባለው በዓል ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘው ተሻገር እንዳሉት የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበር ለአገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና አለው።
በተለይም በዓሉ የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የእርስ በርስ ትውውቅና የባህል ልውውጥ መድረክ ከመሆን ባሻገር የክልሎች መሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ ትልቅ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።
ዕለቱ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ማንነታቸው እንዲከበር ለፍትህ፣ ለነጻነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በጋራ ጠንክረው እንዲሰሩ እንዲሁም በወንድማማችነት እና እህትማማችነት ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ማድረጉንም ተናግረዋል።
አፈ ጉባዔው አክለውም ሰላሟ የፀናና የበለፀገች አገርን ለመፍጠር መላው የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።
19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል።