ቀጥታ፡

የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ አመት የምስረታ በዓል አባላት እና ደጋፊዎች በተገኙበት በጂቡቲ በድምቀት ተከበረ

አዲስ አበባ፤ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ አመት የምስረታ በዓል “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በጂቡቲ የሚኖሩ አባላት እና ደጋፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።


 

ብልጽግና ፓርቲ ቀደም ሲል በአገሪቱ በነበሩት ቁልፍ ችግሮች ምክንያት የተነሳውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የተመሰረተ ፓርቲ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፓርቲው የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ናቸው።


 

ባለፉት አምስት ዓመታት በብዙ ተግዳሮቶች መካከል በጽናት በመስራት ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገበ ፓርቲ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመድረኩም “የህልም ጉልበት ለዕመርታዊ እድገት” በሚል የመወያያ ሰነድ ለታዳሚው የቀረበ ሲሆን፣ ፓርቲው ያጋጠሙት ተግዳሮቶች፣ ያስመዘገባቸው ድሎች፣ አሁን ያሉ ተስፋዎች እና የወደፊት ራዕዩች ላይ በዝርዝር ውይይት ተደርጓል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በግብርና፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ የፕሮጀክት ግንባታ፣ የተቋማት ሪፎርም፣ የቱሪዝም ማስፋፊያ፣ የኢንዱስትሪ ግንባታ እና በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።

የሰላም ጥሪ መሠረታዊ የብልፅግና ፓርቲ አቋም መሆኑን በመግለፅ፥ ህዝባዊ መድረኮች እና ውይይቶች በየደረጃው በማዘጋጀት ብሔራዊ መግግባትን በማምጣት ረገድ በርካታ ስራዎች እንየተሰሩ መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ የወል ትርክቶችን ገዢ በማድረግ እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ በመስራት የአንድነት ተምሳሌት በመሆን ተጀመሩ ስራዎች ይበል የሚያስብሉ እንደሆኑ ተጠቅሷል።

በመቀጠል የፓርቲው 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ በፓርቲው ስም የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ መከናወኑን ከብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም