ቀጥታ፡

የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ቀልጣፋ በማድረግ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን መከላከል የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ቀልጣፋ በማድረግ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን መከላከል የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ። 

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ዓለም አቀፉን የፀረ-ሙስና ቀን አስመልክቶ" ወጣቶችን ያማከለ የፀረ-ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል" በሚል መሪ ሃሳብ በውይይት አክብሯል።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ  የጽህፈት ቤት ሃላፊ አዳነ ሱሌ፤ የመንግስትና የህዝብን ሃብት በመዝረፍ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ከፍተኛ ችግር መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም በገቢዎች ቢሮ በኩል የግብር አሰባሰቡን ቀልጣፋ ከማድረግ ባለፈ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን መከላከል የሚያስችል ስርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።

በሂደቱ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሰራሮችን የመፍጠር፣ ለባለሙያዎች ግንዛቤ የመፍጠርና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የቁጥጥር ስርአት መበጀቱን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት አመት ከ230 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በግብይት ወቅት ደረሰኝ በማይቆርጡ ነጋደዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ከተሳተፉ ሰራተኞች መካከል በሻቱ መንገሻ እና መስከረም ጀማል፤ በጥሩ ስነ ምግባር ግብር ከፋዮችን በማገልገል የግብር መሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም