በክልሉ የኮሪደር ልማት ተሞክሮ ሊሆን የሚችል አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢንጅነር መሀመድ አብዱረህማን - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የኮሪደር ልማት ተሞክሮ ሊሆን የሚችል አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢንጅነር መሀመድ አብዱረህማን
አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- በሀረሪ ክልል የኮሪደር ልማት ስራ ለሌሎች ተሞክሮ ሊሆን የሚችል አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር መሀመድ አብዱረህማን ገለፁ።
የኮሪደር ልማቱ በክልሉ እና አካባቢው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተሳሰር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚኖረው የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናግረዋል።
በኢንጅነር መሀመድ አብዱረህማን የተመራው ቡድን በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
ቡድኑ የመስክ ምልከታውን ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በተገኙበት ከክልሉ ከፍተኛ የስራ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር መሀመድ አብዱረህማን በውይይቱ ላይ እንደገለፁት በክልሉ የኮሪደር ልማት ስራ ልምድ የሚወሰድበት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በተለይ የኮሪደር ልማቱ በከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ጥሩ አፈፃፀም የታየበት መሆኑን መመልከት መቻላቸውን ገልፀዋል።
የኮሪደር ልማቱ የተለያዩ አካባቢዎችን በማገናኘት የመጪውን ግዜ ፍላጎት ከግምት በማስገባት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በተለይ በክልሉ ፖቴንሽያል የሆኑ አካባቢዎችን በኮሪደር ልማቱ ለማገናኘት እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ጠቁመው ጅምር ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ከጉዳት ለመጠበቅ እና ዘላቂ ለማድረግ ከሌሎች የመሠረተ-ልማት አውታሮች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለማከናወን ቅንጅታዊ አሰራር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማቱ ለነዋሪው የተመቸ አካባቢን ለመፍጠር እየተከናወነ እንደሚገኝ በመጠቆም በቀጣይ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ልማቶችን በመደገፍ በጥራት እና ፍጥነት ለማከናወን ከክልሉ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል።
እየተከናወኑ በሚገኙ የኮሪደር ልማቶች መልሶ ማየት የሚገባቸውን ዲዛይኖች ለማስተካከል እንደሚሰራ እና በክልሉ የተመረጡ አካባቢዎችን ለማልማት ወደ ስራ እንደሚገቡም ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ በክልሉ እና አካባቢው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተሳሰር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
በተለይ በኮሪደር ልማት ዘርፍ በፌዴራል ደረጃ ለክልሉ የሚደረገው ድጋፍ ከተማዋን የተሻለ ገፅታ በማላበስ ለኑሮ እና ስራ ምቹ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በፍጥነት ለማከናወን እንደሚያስችል መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።