የኢትዮጵያ አየር ኅይል እመርታ በቀድሞ ባልደረቦቹ አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኅይል እመርታ በቀድሞ ባልደረቦቹ አንደበት
የኢትዮጵያ አየር ኅይል ትናንት 89ኛ የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች መዘከሩ ይታወቃል።
ከዝግጅቱ ታዳሚዎች መካከል የኢትዮጵያ አየር ኅይልን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የሚያውቁት የቀድሞ የአየር ኅይል አብራሪዎችና መምህራን ይገኙበታል።
በ1968 ዓ.ም አየር ኅይልን የተቀላቀሉት የሚግ-243 አብራሪው ኮሎኔል አሰፋ ታደሠ ግማሽ ምዕተ ዓመታት የኢትዮጵያ አየር ኅይልን ያገለገሉ፣ የአየር ሃይልን ከፍታና ዝቅታ ዘመን የታዘቡ መኮንን ናቸው።
የዕውቅ አብራሪዎችን ታሪክ የሚጋሩት ኮሎኔል አሰፋ ታደሠ፤ በአብራሪነት፣ በአቪዬሽን መምህርነት እንዲሁም በድህረ-ጡረታ በሲቪል ሙያ ተመልሰው በአየር ኅይል ዋና አዛዥ አማካሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
ኮሌኔል አሰፋ ካስተማሯቸው አብራሪዎች መካከል ዛሬም በማማከር የሚያገለግሏቸው የወቅቱ የአየር ኅይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ይገኙበታል።
በአፍሪካ ቀዳሚና ስመ-ጥር የነበረው አየር ኅይል ከመንግስት ለውጥ በኋላ የመዳከም ድባብ እንደነበረው አስታውሰው፤ ዛሬ ግን ወደቀደመ ስሙ ትንሳኤውን እያበሰረ መሆኑን ያነሳሉ።
አየር ኅይሉ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በመዘመን ለአፍሪካም ኩራት፤ ለኢትዮጵያም ደጀን የሆነ ተቋም እየተገነባ በመሆኑ ደስታቸው ወደር እንደሌለው ተናግረዋል።
ብርጋዴር ጀኔራል ኃይለሥላሴ ገብሩ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ጡረታ እስከወጡበት 2001 ዓ.ም ድረስ አየር ኅይልን ለሶስት አስርት ዓመታት በአብራሪነትና በመምህርነት ሙያ አገልግለዋል።
ዛሬም ለአየር ኅይል ሙያዊ ድጋፎችን ያደርጋሉ።
በአፄ ኅይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በአፍሪካ ዝነኛ እና ስመጥር ተቋም የነበረ ቢሆንም በጊዜ ሂደት ዝናውን ጠብቆ ባለመሄዱ በተለይም በሰው ሃይልም ሆነ በትጥቁ ሳይዘምን እንደቆየ ገልጸዋል።
ተቋሙ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሰራው ሪፎርም አሁናዊ ቁመናው ቀድሞውኑ ወደሚታወቅበት ከፍታ መመለስ ብቻ ሳይሆን ከዘመኑ ጋር አብሮ እየዘመነ በሁለንተናዊ እመርታ ጎዳና ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የቀድሞ አየር ኅይል የጦር መኮንኖች እንደሚሉት ከአየር ኅይል ለውጥ መገለጫዎች መካከል በራሱ አቅም ሰርቶ ለሁለገብ አገልግሎት የምትውል አውሮፕላን ዝግጁ ማድረጉ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከ89 ዓመታት በፊት በፀሐይ አንድ ፈጠራ የተጀመረው በቴክኖሎጂ ራስን የመቻል ቁጭት፤ ፀሐይ-2ን ዕውን ማድረጉ የአየር ሃይሉን አቅምና ብቃት የሚያሳይ እንደሆነ ነው ያነሱት።
ፀሐይ-2 አውሮፕላን በሰውም፤ ያለሰውም መብረር መቻሏ እንደተደነቁ በመግለጽ፤ አየር ሃይል አሁናዊ አቅሙን ብቻ ሳይሆን የቀጣይ ብሩህ ተስፋውን በጉልህ አመላካች አጋጣሚ እንደሆነ ነው የተናገሩት።