በበጎ ፈቃድ የአይን ብሌንን በመለገስ ለሌሎች ብርሃን ለመሆን የሁላችንም በጎነት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በበጎ ፈቃድ የአይን ብሌንን በመለገስ ለሌሎች ብርሃን ለመሆን የሁላችንም በጎነት ያስፈልጋል
በበጎ ፈቃድ የአይን ብሌንን በመለገስ ለሌሎች ብርሃን ለመሆን የሁሉም በጎነት አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የአይን ብሌን ልገሳን በተመለከተ ከተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው፤ ከተቋቋመ 21 ዓመት የሞላው የአይን ባንክ በ2015 ዓ.ም ከደም ባንክ ጋር በመዋህድ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በሚል ስያሜ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከበጎ ፈቃደኞች የአይን ብሌን በማሰባሰብና በማስተባበር ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸው ማየት ለሚችሉ ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ ለሆስፒታሎች እየሰጠ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በ20 ዓመታትም ለ3 ሺህ ዜጎች የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸው የአይን ብርሃን ማግኘት መቻላቸውን አስታውቀዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በአመት በአማካይ ለ295 ዜጎች የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ እንዲደረግላቸው እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ለመለገስ ቃል የገቡት በጎ ፈቃደኞች ቁጥር ግን 15 ሺህ ብቻ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በመሆኑም ከህክምና ፈላጊዎቹ አንፃር የለጋሾቹ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በቀጣይ የአይን ብሌን ልገሳን አስፈላጊነት በስፋት የማስገንዘብ ስራ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።
በበጎ ፈቃድ የአይን ብሌንን በመለገስ ለሌሎች ብርሃን ለመሆን የሁላችንም በጎነት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩም 74 የሚሆኑት ከህልፈት በኋላ የአይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡