የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አራተኛውን የኮርያ አምባሳደር ካፕ ውድድር ማካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አራተኛውን የኮርያ አምባሳደር ካፕ ውድድር ማካሄድ ጀምሯል።

ውድድሩ ከኅዳር 19 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ ''እኛ የቴኳንዶ ቤተሰቦች ነን " በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ ይገኛል።

በውድድሩ ማስጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ጁንክ እንደገለፁት፤ ይህ ውድድር ለወጣት ኢትዮጵያውያን የቴኳንዶ ተወዳዳሪዎች  ብቃታቸውን በተሟላ ሁኔታ የሚያሳዩበት ነው።

በተጨማሪም ውድድሩ ከዓለም ዙሪያ ካሉ የቴኳንዶ ባለሙያዎች ጋር የሚገናኙበት በመሆኑ፤ ጓደኝነትን የሚፈጥሩበትና  ልምድ የሚያገኙበት እንደሆነም ገልፀዋል። 

ለኢትዮጵያ የቴኳንዶ ዕድገትም አዲስ ምዕራፍ  እንደሚከፍትና፤ የሁለቱ አገራት ወዳጅነትና ግንኙነት እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኃይሉ ጉተታ በበኩላቸው፤ ወርልድ ቴኳንዶ የኦሊምፒክ ስፖርት እንደሆነ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በስፖርቱ ውጤታማ እንድትሆንና ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት እንድትችል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጠንካራ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እንደነዚህ ዓይነት ውድድሮችም ለብሔራዊ ቡድን የሚመረጡ የዘርፉን ስፖርተኞች ለመለየትም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

አራተኛው የኮርያ አምባሳደር ካፕ ውድድር በሦስት የውድድር ዓይነቶች እየተከናወነ ሲሆን ፍልሚያ (ፋይት)፤ አርት ፑምሴና ኤሮቢክ ናቸው።

በውድድሩ ሰባት ክልሎች፤ ሁለት ከተማ መስተዳድሮች፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚና፤ ጅቡቲ እየተሳተፉበት ነው። 

ውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች እየተከናወነ ሲሆን በወንድ 186 በሴት ደግሞ 82 ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉበት ይገኛል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም