ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በቅርስ ጥበቃና አያያዝ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በቅርስ ጥበቃና አያያዝ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

የፈረንሳይ የአውሮፓ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምንና በፈረንሳይ መንግሥት የተመሠረተውን የሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

ሚኒስትር ጂያን ኖኤል ባሮት በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1960ዎቹ ከመልካ ቁንጥሬ መካነ ቅርስ ለምርምር ወደ ፈረንሳይ ተወስደው የነበሩ ጥንታዊ የሰው ዘር የተገለገለባቸውን የድንጋይ መሣሪያዎች ለቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ አስረክበዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ያላትና የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።

የፈረንሳይ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሀገሪቱ የገቡ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ማድረጉ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።

በመርሃ-ግብሩ በፈረንሳይ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚተገበር ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።

ይህ ፕሮጀክት ይፋ መደረጉ ሁለቱ ሀገራት በቅርስ ጥበቃና አያያዝ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያደርጋቸው እንደሆነም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

የፈረንሳይ የአውሮፓ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮት በበኩላቸው፤ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።

እ.አ.አ በ2019 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በደረሱት ስምምነት መሠረት የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያንና የብሔራዊ ሙዚየም እድሳት ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

በቀጣይም ፈረንሳይ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክትን በመተግበር ሁለቱ ሀገራት በዘርፉ የሚኖራቸውን አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም