ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በማስተሳሰር ለምጣኔ ሃብት እድገት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አህጉርን በማስተሳሰር ለምጣኔ ሃብት እድገት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ በ2020 አቋርጦት የነበረውን ከአዲስ አበባ ወደ ሞንሮቪያ የቀጥታ በረራ በዛሬው ዕለት ዳግም ጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት አየር መንገዱ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስርን የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው።

ወደ ሞንሮቪያ የዳግም በረራ መጀመሩ እንዲሁም በቅርቡ ወደ ባንግላዲሽ ዳካና ፖርት ሱዳን አዳዲስ መዳረሻ መፍጠሩ የአየር መንገዱን ሚና የሚያሳድግ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካውያንን በአየር ትራንስፖርት ለማስተሳሰር እየሰራ ሲሆን ላይቤሪያ በአፍሪካ ካሉት ሀገራት 41ኛ በከተማ ደረጃ ደግሞ ሞንሮቪያ 63ኛ መዳረሻ ሆነዋል ብለዋል።

ይህም የቱሪዝም፣ የንግድ፣ የሰዎች እንቅስቃሴን በማሳለጥ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲ የአገራትን ትብብርና ተጠቃሚነት በማሳደግ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል። 

ወደ ሞንሮቪያ በሳምንት ሶስት ጊዜ የሚያደርገው ቀጥታ በረራ እንግልትን እንደሚያስቀር ዋና ስራ አስፈጻሚው አመላክተዋል።

በተመሳሳይ በሁለቱ አገራት መካከል የመንግስታት፣ የባህል፣ የህዝብ ለህዝብና ምጣኔ ሃብት ትስስርን የበለጠ እንደሚያጠናክር ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካውያን በሚሰጠው የመንገደኞች እንዲሁም የጭነት አገልግሎት ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

የላይቤሪያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሲርሊፍ ታይለር በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም ወደ ላይቤሪያ በረራ መጀመሩ አገሪቱን ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር ያገናኛታል ብለዋል።

አየር መንገዱ በአህጉሪቱ የምጣኔ ሃብት እድገት ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አድንቀው፥ በላይቤሪያና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ አስታውቀዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም