ብልጽግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት ለትውልድ የሚሸጋገሩ ድሎችን አስመዝግቧል- የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት ለትውልድ የሚሸጋገሩ ድሎችን አስመዝግቧል- የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- ብልጽግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያን ስብራቶች ከመጠገን ባሻገር ለትውልድ የሚሸጋገሩ ድሎችን አስመዝግቧል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
“የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር በአደዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩም የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የፓርቲው አባላት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል፡፡
የፓርቲው ፕሬዝዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ካላት ቁርጠኝነት አንጻር ብልጽግናን ማረጋገጥ የሁሉም ዜጎች የወል እውነት ነው ብለዋል፡፡
ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ብሔራዊ ወንድማማችነት እንዲሁም እውነት፣ እውቀትና ጥበብን መለያው አድርጎ ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል ነው ያሉት፡፡
ብልጽግናን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያዊያን የያዝነው ራዕይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ፓርቲዎች እንዳይሳካላቸው ያደረጉ አምስት ዋና ዋና ስብራቶች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡
እነዚህም ሙሉ ለሙሉ ከውጭ የተቀዳ ርዕዮት ዓለም፣ ኃይልና ሃሳብን መቀላቀል፣ የወዳጅና ጠላት ፖለቲካ፣ አካታች አለመሆን እንዲሁም የዴሞክራሲ እጥረት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ከእነዚህ ስብራቶች ትምህርት በመውሰድ ሀገር የሚያሻግር ተራማጅ ፓርቲ መሆን መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
"የሃሳብ ልዕልና" የሚለው እሳቤም የብልጽግና መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፖለቲካ የኃይል ሳይሆን የሃሳብ ሜዳ ብቻ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ሃሳብን በሃሳብ እንጂ በኃይል ማሸነፍ እንደማይቻል አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ፈተናዎችን አዲስ በሆነ አካሄድ ለመፍታት የሄደባቸው ርቀቶች ስኬታማ እንደነበሩም ነው የተናገሩት፡፡
በቀጣይም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በሪፎርም፣ በንግግር፡ በሽግግር ፍትህ፣ ሰጥቶ በመቀበል እና በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አውስተዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም በኃይል የሚያሳኩት ምንም አይነት ነገር አለመኖሩን ገልጸው፤ መንግስት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ቁርጠኛ በመሆኑ ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች በርካታ ድሎችን ማስመዝገቡን አንስተው፤ ለአብነትም የኢትዮጵያን ጥቅል ዓመታዊ እድገት በአጠረ ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ዓምስት ዓመታት ደግሞ አሁን ያለውን ጥቅል ዓመታዊ አድገት በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ 5 ዓመታት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ዜጎች በተደመረ አቅም ሀገራቸውን የሚያሳድጉበት እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከፓርቲው ጎን ተሰልፈው የተሻለ ስኬት እንዲመዘገብ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡