በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተናል- የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተናል- የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች
አርባምንጭ ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- በአርባምንጭ ከተማ በሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ መሆናቸውን የከተማው አስተዳደርና ነዋሪዎች ገለጹ።
"አገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት"በሚል መሪ ሀሳብ በዓሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29/2017 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ ይከበራል።
ዝግጅቱን አስመልክቶ ኢዜአ ካነጋገራቸው መካከል የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ መተኪያ አበበ ፤ 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።
በከተማው የተለያዩ ማህበራዊ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ከተማዋን የማስዋብ እንዲሁም የጽዳትና የውበት ሥራዎች በከፍተኛ ሞራልና ተሳትፎ መከናወኑን ተናግረዋል ።
አርባምንጭ የሰላምና የመቻቻል ከተማ ከመሆኗም በላይ ሰፊ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ያሉባት ናት፤ ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶች እርካታ አግኝተው ጥሩ ጊዜ ያሳልፋሉ ብለዋል።
ለእንግዶቹ ማረፊያ የሚሆኑ ሆቴሎች፣ ሎጆችና ሪዞርቶች በበቂ ሁኔታ ዝግጅት አጠናቀው እንግዶችን እየጠበቁ መሆናቸውንም አቶ መተኪያ ገልጸዋል።
የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪ አቶ አድነው በዛብህ በበኩላቸው፤ 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔርሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶች ይህን ታላቅ ኩነት በደስታ እንድያከብሩ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የበዓሉ መከበር የህዝቡን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር ባህላዊ እሴቶችን ለመለዋወጥ ልዩ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የጋሞ ዞን ህዝብ እንግዳ ተቀባይ ሰው አክባሪና ፀብን በእርጥብ ሣር የሚያበርድ ማህበረሰብ መሆኑን በመጥቀስ " እንግዶችን በጨዋ ባህላችን ለመቀበል ተዘጋጅተናል " ያለው ደግሞ ወጣት ሙሴ ከበደ ነው።
በዓሉን ለማክበር የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት ወደሆነችው አርባምንጭ ከተማ የሚመጡ እንግዶች በደስታ ማሳለፍ እንዲችሉ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል።
ባሉን አደረጃጀቶች ሁሉንም የከተማዋን አከባቢ ከማስዋብ ጀምሮ የተለያዩ የጸጥታና ሰለም ማስጠበቅ ስራዎችን ከፖሊስ ጎን በመሆን እየሰራን ነው ብሏል።
ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ መምህርት ቦጋለች ኤሊያስ ወትሮም፤ ውብና ሰላም የሆነችውን የአርባምንጭ ከተማ የተለያዩ የጽዳትና የውበት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ከተማዋን ይበልጥ ውብ እና ለእንግዶች ምቹ አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።
"አገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት"በሚል መሪ ሀሳብ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ህዳር 29/2017 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ ይከበራል።