ቃልን በተግባር መፈጸም የብልጽግና ተጨባጭ መለያዎቹ ናቸው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ቃልን በተግባር መፈጸም የብልጽግና ተጨባጭ መለያዎቹ ናቸው - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- ቃልን በተግባር መፈጸም የብልጽግና ተጨባጭ መለያዎቹ ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ አመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሀ-ግብር በአድዋ መታሰቢያ ተካሂዷል።
በመርሀግብሩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ እንዲሁም የፓርቲውና የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተከብሯል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት የበአሉ አላማ ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ያደረገውን ጉዞ ለመዘከር እና ቃላችንን ለማደስ ነው ብለዋል።
ፓርቲው በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም እነዚህን ፈተናዎች ወደ ድል በመቀየር አንጸባራቂ ድል ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
የትግላችን መዳረሻ ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቃልን በተግባር መፈጸም የብልጽግና ተጨባጭ መለያዎቹ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት አምስት አመታት በሁሉም ዘርፍ የታሪክ እጥፋት የተመዘገበበት መሆኑን ማመላከታቸውን ከፓርቲው ማህብራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው በተገኙ ውጤቶች ሳንዘናጋ ውጤቶቻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ አመት የምስረታ በዓል "የሀሳብ ልእልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል።