ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን የትብብር አድማስ ለማስፋት እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ለማስፋት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን የንግድ ሚኒስትር ጃም ከማል ካን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሁለቱ አገራት የጋራ ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ በንግዱ ዘርፍ በተለይም በአገራቱ የንግድ ማህበረሰብ መካከል ያለውን የንግድ ትስስርን ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

አምባሳደሩ ለሚኒስትሩ ስለ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የግብርና ምርታማነት ስራዎች፣ የንግድ ስራ ምቹነትን ለማሻሻልና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ኢትዮጵያና ፓኪስታን ንግድ፣ ባህል፣ አቪዬሽን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸው የሁለትዮሽ ትብብር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል በተለያዩ መስኮች ለመስራት የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ የጀመረው በረራ እና የአገራቱ ልዑካን ቡድን ጉብኝቶች ትስስሩን ይበልጥ እንዳጠናከረው አመልክተዋል። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ በር ናት ያሉት አምባሳደሩ በዚህ ረገድም የኢትዮጵያን ምርቶች እና አገልግሎት የሚያስተዋውቅ ኤግዚቢሽን (Single Country Exhibition) በአዲስ አበባ ቢዘጋጅ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

የኤግዚቢሽኑ መዘጋጀት የፓኪስታን ባለሀብቶች ከኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ ባለፈ ከአፍሪካ ገበያ ጋር እንዲተሳሰሩ ምቹ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የፓኪስታን የንግድ ሚኒስትር ጃም ከማል ካን ሚኒስቴሩ እና የፓኪስታን የንግድ ልማት ባለስልጣን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽኑ እንዲካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል ።

ፓኪስታን “Look Africa and Engage Africa Policy” የፖሊሲ ማዕቀፏ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ሚኒስትር ካን የአፍሪካ የእድገት ኮከብ የሆነችው ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራርነት የማይበገር ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን መግለጻቸውን በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም