የኮሪደር ልማቱን ተከትለው የተገነቡ ዘመናዊ መኪና ማቆሚያዎች ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ማግኘት አስችሎናል - አሽከርካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቱን ተከትለው የተገነቡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀ የፓርኪንግ አገልግሎት ማግኘት አስችሎናል ሲሉ አሽከርካሪዎች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ በማስዋብና ለነዋሪዎች ምቹ መኖሪያ ከማድረግ ባለፈ ጥሩ የመዝናኛ አማራጮች እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ 


 

አዲስ አበባን የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የሚመጥን የክትመት ደረጃ ላይ እንድትገኝ እያደረጋት መሆኑም ይታወቃል።

በከተማዋ በተለይም የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተገነቡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች የተመቸና አስተማማኝ ፓርኪንግ እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።

በተጨማሪም ውበትና የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ማሰቻላቻውን አሽከርካሪዎች ይናገራሉ፡፡

ከአሽከርካሪዎቹ መካከል ዮሴፍ ይልማ፣ ታዲዮስ ዘውገ እና ሰለሞን ጸጋዬ፤ በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም የመኪና ማቆሚያ ችግር እንደነበረ አንስተዋል፡፡

የነበሩትም ቢሆኑ ደህንነታቸው አስተማማኝ አልነበሩም ሲሉ ተናግረዋል ።

 የኮሪደር ልማቱን ተከትለው  ዘመናዊ መኪና ማቆሚያዎች መገንባታቸው ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ማግኘት አስችሎናል ሲሉ አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የፓርኪንግና የትራፊክ መሰረተ ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር ቢንያም ጌታቸው፤ በመዲናዋ እየጨመረ የመጣውን የተሽከርካሪ ቁጥር የሚመጥኑ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመኪና ማቆሚያዎቹ የተሳለጠ የትራንስፖርት ፍሰት ከመፍጠር ባለፈ ለመዲናዋ ዘመናዊነትና ውብ ገጽታም ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ አሁን ላይ በአንድ ጊዜ ከ6 ሺ በላይ ተሸከርካሪዎችን ማቆም የሚችሉ 45 ዘመናዊ ፓርኪንጎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም