የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቀን አንድነታችን እንዲጠናከርና እሴቶቻችን ጐልተው እንዲወጡ አድርጓል -- አፈ ጉባዔዎች - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቀን አንድነታችን እንዲጠናከርና እሴቶቻችን ጐልተው እንዲወጡ አድርጓል -- አፈ ጉባዔዎች
ሠመራ ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቀን አንድነታችን እንዲጠናከርና እሴቶቻችን ጎልተው እንዲወጡ አድርጓል ሲሉ የክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈ ጉባዔዎች ተናገሩ።
የክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች የተሳተፉበት 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "አገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በሠመራ ከተማ ተከብሯል ።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት /ጨፌ ኦሮሚያ/ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ''የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ጥላ ሥር እንድንሰባሰብ አድርጎናል'' ብለዋል።
ቀኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኩራት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና የአኗኗር ዘይቤያቸውን በማስተዋወቅ አንድነትን ለማጠናከር ዕድል እንደፈጠረ ገልጸዋል።
የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድነት ተሰባስበውና ደምቀው የታዩበትን በዓል በጋራ በማሳለፋቸው ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ''በዓሉ ባህላችን፣ ወጋችንና ማንነታችንን እየገለፅን በኩራት የምናከብረው ነው'' ብለዋል።
የበለፀገች ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት መሠረት መሆኑንም አክለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር በዓሉ የኢትዮጵያ ብልጽግና ተስፋ ከሚታይባቸው ክልሎች አንዱ በሆነው በአፋር ክልል በጋራ ማክበራቸው ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ክልሉ ከሚታወቅበት ጨው ምርት በተጨማሪ በአረንጓዴ የልማት ሥራዎች በማከናወን ለብልፅግና ተጨማሪ የሆነ ተሰፋ የፈነጠቀ ክልል መሆኑን በማመላከት።
በዓሉ በአፋር ክልል ደረጃ የተከበረው 19ኛው ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ማጠቃለያ መድረክ መሆኑም ተመላክቷል።