ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የወታደራዊ ሳይንስና የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ማዕከል ነው - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ችግሮችን በማለፍ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ የሚገኝ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ የሳይንስና የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ማዕከል መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) የተመራ የኮሚቴው አባላት የዩኒቨርሲቲውን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

የምክር ቤቱ አባላት የትምህርት ፕሮግራሞችን፣ የሳይንስ ተኮር የቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶችና የግብርና ፈጠራ የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጀኔራር ከበደ ረጋሳ ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ያላቸውን ስራዎች አስመልክቶ ለምክር ቤቱ አባላት ገለጻ አድርገዋል።

ዩኒቨርሲቲው የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የልህቀት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ዩኒቨርሲቲው የመከላከያ ሠራዊት አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወዳዳሪነት ሚናውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር እያከናወነ ያለውን ስራ አድንቀዋል።

የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶች እንደ ሀገር ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸው ዩኒቨርሲቲውን መደገፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው እየሰራቸው የሚገኙ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ስራዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር በዘላቂነት የሚፈቱና ተጠቃሚ እያደረጉ የሚገኙ በመሆናቸው የአለኝታነት ሚናውን በተግባር እየተወጣ ነው ብለዋል።

ብቸኛው የኢትዮጵያ ወታደራዊ የትምህርት ተቋም የሆነውን ዩኒቨርሲቲ የመከላከያ ሰራዊቱን ዓለም አቀፋዊ የልህቀት ተወዳዳሪነት በሚመጥን አግባብ ስራውን እንዲያከናውን ድጋፍ እንደሚያሻው ነው የምክር ቤቱ አባላት የገለጹት።

ምክር ቤቱ ዩኒቨርሲቲው ለሚያከናውናቸው ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

ለሀገር ክብር እና ለመከላከያ ሰራዊት እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመበት የአዋጅ ደንብም እንደገና ለአሰራር በሚያመች አግባብ መልሶ እንዲታይ የምክር ቤቱ አባላት ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም